በሀገራዊ ምክክር ሂደት በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ ለሴቶች ተገቢ ውክልና ትኩረት መስጠት ይገባል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ 35 አባላትን ያቀፈ የአማካሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ኮሚሽኑ በኮሚቴው እንዲካተቱ የጋበዛቸው ግለሰቦች በተለያየ መልኩ ለኮሚሽኑ ሥራዎች ድጋፎችን የሚያደርጉ ሲሆን በተለያየ ልምድ እና ሙያ ውስጥ እንዳሉም ተገልጿል፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እንዲሁም በምክክር ሂደት ላይ ሥራዎችን ያከናወኑ ግለሰቦች እና የተቋማት ተወካዮች የኮሚቴው አባላት ሆነው ተካትተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ኮሚቴ ሲያዋቅር በተቋቋመበት አዋጅ 1265/2014 ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን መሠረት አድርጎ ለኮሚቴው ሥራዎችን የሚያከናውንበትን የውስጥ መመሪያ ማዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት የተቋቋመው ኮሚቴ ኮሚሽኑ በአዋጅ እንዲሠራ የተሰጠውን ተግባራት እና ሓላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ ኮሚሽኑን በተለያዩ ዘርፎች በማማከር እገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ አዋጁ ሴቶች በሁሉም ዓይነት አገራዊ ውይይቶች ላይ እኩል ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ቢገልጽም፣ 35 አባላት በያዘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካሪ ስብስብ ውስጥ የተካተቱት ሴቶች ቁጥር ሲታይ ውክልና ተሰጥቷቸዋል የሚባል አይደለም።
ከአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር 50 በመቶ በላይ ሴቶች በሆኑባት ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሚሽኑ አማካሪ ኮሚቴ ውስጥ ያሉት ሴቶች ውክልና እንኳን ግማሽ ያህል ቀርቶ ለዓይን የሚሞላ ሆኖ አይታይም። ይህም ትልቅ የአካታችነት ክፍተት መኖሩን ያሳያል። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 2(6) መሠረት ሰው የሚለው ቃል ወንድ እና ሴትን ያጠቃልላል። በዚህም ሴቶች በአገራዊ ውይይት ላይ እኩል ተሳትፎ እንደሚኖራቸው መረዳት እንችላለን። ከዚህ ጎን ለጎን በአዋጁ አንቀጽ 3(ሀ) ላይ ኮሚሽኑ እየተጠቀመባቸው ያሉ መርሆዎች መካከል የመጀመሪያው አካታችነት ነው። ማካተት በቡድን ወይም መዋቅር ውስጥ የማካተት ወይም የመካተቱ ተግባር ወይም ሁኔታን የሚያመለክት ነው።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ሥርዓተ-ጾታን እና የማኅበረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ግልጽ እና አካታች እንዲሆን እንዲሁም በተቀላጠፈ መልኩ እንዲካሄድ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በዚህ የአቋም መግለጫ ላይ የሥርዓተ-ጾታ አማካሪዎች በሁሉም የኮሚሽኑ የአሠራር ሂደት ቀረጻ፣ ቴክኒካዊ ቡድኖች አወቃቀር፣ የውይይቶች አካሄድን ጨምሮ በእያንዳንዱ የምክክሩ ሥራዎች ውስጥ እንዲካተቱ መጠየቃችን እንዲሁም የምክክሩን ሂደት የሴቶችን እኩል ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት፣ የሥርዓተ-ጾታ አካታችነትን ያረጋገጠ ለማድረግ ጥምረታችን ግንባር ቀደም ሆኖ ለመሥራት የተዘጋጀ በመሆኑ በሂደቱ አብረው መሥራት የሚችሉ ባለሙያዎችንና አሠራሮችን በመለየት ረገድ ኮሚሽኑን ለማማከር እና የሚጠበቅብንን ሓላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ገልጸናል።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ቦርድ ውስጥ ሴቶች በእኩልነት እንዳልተወከሉ ያምናል። እኩል ውክልና እና የሴቶች በፖለቲካ ውስጥ መካተት አድልኦ ለመቀነስ እና የበለጠ እኩል የሆነ ዓለም ለመፍጠር የመንግሥትም ሆነ የግሉ ሴክተሮች ልዩነቶችን መፍታት እና ጾታን ማካተት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል የሚል እምነት አለው። ምክንያቱም የሴቶች በፖለቲካ ውስጥ መካተት ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለመላው ማኅበረሰባቸው ጠቃሚ በመሆኑ ነው።
ይህም ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሴቶች ውክልና ኢ-ፍትሐዊነት ላይ ስናነሣቸው የነበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ ያላገኙ ለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው። በመሆኑም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እመራባቸዋለሁ በሚል ካወጣቸው ጉዳዮች መካከል አካታችነት እና ፍትሐዊነትን በየደረጃው በሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ለሴቶች ተገቢ ውክልና እንዲሰጥ በድጋሚ እንጠይቃለን።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክከር መድረክ
ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ