Timran

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ መሳተፍ እንዲችሉ የሚያስችል የሦስት ቀናት አቅም የመፍጠር መድረክ በጥምረት ለሴቶች ድምፅ አዘጋጅነት በድሬዋዳ ከተማ ተጀመረ

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ መሳተፍ እንዲችሉ የሚያስችል አቅም የመፍጠር መድረክ በጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ እና ትምራን የተዘጋጀ የሦስት ቀናት የምክክር መድረክ በድሬዋዳ ከተማ መጋቢት 06 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ ተጀምሯል።

የመጀመሪያ ቀን ምክክር መድረክ ላይ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የሴቶች ፌዴሬሽን፣ ሴት አካል ጉዳተኞች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ የቤት እመቤቶች፣ ሴት የእድር አባላት፣ የሲቪክ ማኅበራት ሴት አባላት፣ ሴት ወጣቶች እና ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ትምራንን ጨምሮ ከ50 በላይ የሚሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት መሆኑን ገልጸዋል።

ጥምረቱ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ የሴቶች ውክልና እና ተሳትፎ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት ይህም በሀገር ደረጃ ሴቷ ድምጿ እንዲሰማ እና የራሷ አጀንዳ ያላት መሆኑ እንዲታወቅ የውትወታ ሥራ እንደሚሠራ  ተናግረዋል።

በድሬዳዋ የተጀመረው የሴቶችን አቅም የማጎልበት ተግባር ጥምረቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያከናውናቸው መድረኮች መካከል የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመው፣ በመድረኩ ላይ የሚነሡ ሐሳቦች ሴቶች ወደፊት የምክክር ኮሚሽኑ በሚያደርገው ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ይህንን ሂደት የማገዝ፣  በቀጣይ በሚደረጉ ሀገራዊ የምክክር እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የማንቃት እና መሰል ውይይቶችን በየአካባቢዎች የማዘጋጀት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በቀጣይ ቀናት ከድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች ልዩ፣ልዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ሴቶች እንዲሁም የመስተዳድር አካላትን ጨምሮ በተለያዩ የሞያ መስኮች የተሰማሩ ሴቶች የሚሳተፉባቸው መድረኮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts

Archives


Categories