Timran

በሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ሴቶች ያላቸው ውክልና ምን ይመስላል በሚል ጭብጥ የዙም ውይይት ተካሄደ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ሴቶች ያላቸው ውክልና ምን ይመስላል በሚል ጭብጥ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በየሳምንቱ በሚያዘጋጀው ‘ሴቶች ተኮር’ የዙም ውይይት አማካኝነት ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሄደ።

መርሐ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ሥራ አስኪያጅ እና የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ ሳባ ገብረ መድኅን፣ ድርጅታቸው በየሳምንቱ በሚያካሄደው የዙም ውይይት ላይ ሴቶች የሀገር ሰላምን ጨምሮ በየዘርፉ ያላቸው አበርክቶ በተመለከተ ሐሳቦች እንደሚንሸራሸሩ ገልጸዋል።

ሴቶች በሀገራዊ ምክክር መድረክ ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ትምራን ባዘጋጀችው የውይይት ጉባኤ ላይ ከአንድ ዓመት በፊት በ22 መሥራች ድርጅቶች መመሥረቱንና በአኹኑ ወቅት ከ50 ያላነሱ አባል ድርጅቶች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

ጥምረቱ በሥራ አፈጻሚ ኮሚቴ የሚመራ መኾኑንና ከሴቶች ተሳትፎ ጋር በተያያዘ በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጥምረቱን አጠቃላይ የአንድ ዓመት በላይ ጉዞ በተመለከተ ገለጻ የሰጡት ጥምረቱን በጽ/ቤትነት እያገለገለች የምትገኘው የትምራን ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ በበኩላቸው፣ ጥምረቱ ከምሥረታ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያከናወናቸውን ተግባራት እና የያዛቸውን እቅዶች አብራርተዋል።

የጥምረቱ ምሥረታን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በርካታ የትብብር ሥራዎች እየሠራ መኾኑን በዝርዝር አስረድተዋል።

ጥምረቱን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ማስተዋወቅ፣ ሐሳቦች በማፍለቅ እና ሰነድ በማዘጋጀት ለጋሾች ማፈላለግ፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር ምንነት ላይ የውይይት መድረኮች ማዘጋጀት፣ የጥምረቱ አባላት ሀገራዊ ምክክር ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ልምድ ካላቸው ጎረቤት ሀገራት ተሞክሮ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የጥምረቱን የዕለት ተዕለት ተግባራት የሚያከናውኑ ባለሞያዎች ቅጥር መፈጸም እና ከጥምረቱ ጋር አብረው ሊሠሩ የሚችሉ የባለድርሻ አካላት ዳሰሳ ጥናት ማከናወኑን አመልክተዋል።

አክለውም የጥምረቱ አባላት መመሪያ ብሎም የተግባቦት እና ውትወታ ሰነዶች ማዘጋጀት፣ ሴቶች ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል የአመቻች ሰነድ ማዘጋጀት፣ ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ ቁጥራቸው 152 የኾኑ ሴቶችን የአመቻችነት የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠት፣ ስለ ሀገራዊ ምክክር ለኅብረተሰቡ በሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሐሳብ ማፍለቅ እና መረጃ ማጥራት መድረኮች ማካሄድ መቻሉን ዘርዝረዋል።
ከዚኽ ባሻገር ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ እና ሲዳማ ክልሎች አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በጠቅላላ ከ2000 በላይ ሴቶች የተሳተፉባቸው በርካታ የውይይት መድረኮች በማከናወን ሴቶች በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሐሳቦች እንዲያንፀባርቁ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በጥቅሉ ጥምረቱ በተገባደደው ዓመት ውስጥ 11 ተግባራት ለማከናወን አቅዶ ዘጠኙን መፈጸም መቻሉን ጠቅሰዋል።

ጥምረቱ እነዚኽን ተግባራት ሲያከናውን በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም እና መረጋጋት መጥፋቱ ፈታኝ ኹኔታ እንደነበር ሥራ አስፈጻሚዋ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ተከታታይ የሴቶች ምክክር መድረኮች ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በቀሪዎቹ ክልሎችም ተመሳሳይ መድረኮች ለማከናወን ደጋፊ አካላት በማፈላለግ ላይ እንደኾነ ተናግረዋል።

የተሰጠውን ማብራሪያ ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሎች በተካሄዱ ምክክር መድረኮች ላይ ሴቶች የተሳተፉባቸው መስፈርቶች፣ የተሳታፊ ሴቶች ስሜት ምን ይመስል እንደነበር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች ለሚገኙ ሴቶች መሰል የምክክር መድረኮች እስካኹን የዘገዩት ለምን እንደኾነ፣ ጥምረቱ ያስጠናው የባለድርሻ አካላት ትንተና ሰነድ ውጤት ምን እንደሚመስል፣ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የበለጠ እንዲጨምር ብሎም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የምክክር ተሳታፊ ልየታባከናወነባቸው ክልሎች የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ በመኾኑ በጥምረቱ በኩል ምን ለማድረግ እንደታሰበ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እና ሐሳቦች ተነሥተዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ማኅደር ዳዲ ጥምረቱ በቀጣይ በያዛቸው እቅዶች ውስጥ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንደሚያገኙ፣ በዚኽ ዘመን የተገኘውን ሀገራዊ ምክክር ጨምሮ በኹሉም የሕይወት መስክ ውስጥ ሴቶች ተገቢ ውክልና እና ተሳትፎ እንዲያኖራቸው ለማስቻል የጋራ ርብርብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts