Timran

በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮች ኅብረት የመጀመሪያ ዙር ስብሰባ ተካሄደ

ትምራን ያዘጋጀችው በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮች ኅብረት የመጀመሪያ ዙር ስብሰባ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሄደ።

መድረኩን የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ትምራን ከአራት ዓመት ገደማ በፊት በሀገሪቱ ያለውን የሴት አመራሮች ክፍተት ለመሙላት የተቋቋመች ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር መኾኗን ተናግረዋል።

ትምራን ሴቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ብሎም በየትኛውም የሥራ መስክ በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ ለማስቻል ከምታከናውናቸው ተግባራት መካከል የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በዚኽም መሠረት ሴቷ ሰላምን ትምራ በሚለው ፕሮጀክቷ አማካኝነት ባለፈው ዓመት በስምንት ክልሎች የሴቶች የሰላም መድረኮች ማዘጋጀቷን ገልጸው፣ በእነዚያ መድረኮች የተገኙ ግብአቶችን መሠረት በማድረግ የዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ሴት አመራሮች ኅብረቶች የመመሥረት ተግባራት እያከናወነች እንደኾነ አመልክተዋል።

በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮች ኅብረት ከአራት ወር በፊት የተመሠረተ ሲኾን፣ የመጀመሪያውን ስልታዊ ስብሰባ ለማካሄድ ለተገኙ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

በመቀጠል ኅብረቱ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት በቀጣይ ሊሠራባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የባለሞያ መነሻ ሐሳብ ቀርቦ የቡድን ውይይት እና ገለጻ ተደርጓል።

በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮች ኅብረት የመጀመሪያ ዙር ስብሰባ ኅብረቱን የሚመሩ ተወካዮች የመረጠ ሲኾን፣ በቀጣይ በዝቅተኛ እንዲኹም በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙ ሴት አመራሮች ጋር በጥምረት ለመሥራት ትምራን መድረክ እንድታመቻች ጠይቋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts