Timran

በሰላም እና በዴሞክራሲ ላይ የሚሠሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተካተቱበት የኢትዮጵያ የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ተመሠረተ

በምሥረታው ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታየ ደንደዓን ጨምሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረቱ አባላት እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በዕለቱ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ኅብረቱ በሰላም እና በግጭት አፈታት ላይ የሚሠራ በመሆኑ ትልቅ ዓላማ ይዞ ተነሥቷል፤ የሰላም ሚኒስቴርም በሰላም እና በሀገር ግንባታ ላይ ከኅብረቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ያለ ሰላም መሥራት አይቻልም፤ የተሠራውንም መጠበቅ አይቻልም ያሉት አቶ ታዬ በተለይ አሁን ባለንበት ወቅት ከሰላም የበለጠ አጀንዳ እንደሌለ ገልጸው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚህ ረገድ በርካታ ሊሠሯቸው የሚገቡ ሥራዎች መኖራቸውን አንሥተዋል፡፡ ሰላም ስለተፈለገ በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም፤ የረጅም ጊዜ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን፣ በውይይት እና በንግግር ችግሮቻችን የሚፈቱበትን ዐውድ መፍጠር አስፈላጊ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው ሰላምን ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ ሚና ካላቸው ተዋናዮች መካከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን አንሥተው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ በተለይም ጠንካራ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አንሥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እንዲገነባ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ በትብብር መሥራት፣ በሰላም ግንባታ ላይ ጥናቶች ማድረግ፣ ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል እና ግጭቶች በተከሰቱ ጊዜም በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን ስልት ለመቀየስ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ኅብረት እንደ መሆኑ መጠን እንደ ሀገር ላለምነው ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኅብረቱ ሰላምን ለማስጠበቅ አግባብ ካላቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት አካላት ጋር በመተባበር የአገር እና ሕዝብ ሰላም እንዲከበር ስልት መቀየስ፣ የግንዛቤ እና የንቅናቄ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከሚመለከታቸው የክልል ባለድርሻ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በሁሉም የአገሪቱ ክልል ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት እንዲችሉ እና ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ ድጋፍ ማድረግ፣ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም እምነቶች መካከል ሰላም እና መከባበር እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ኅብረቱ ሚናውን በሚገባ እንደሚወጣ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ኅብረቱ በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በቅርበት የሚደግፍ መሆኑን ያነሡት ዋና ዳይሬክተሩ ለሰላም ግንባታ አጋዥ የሆኑ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በመለየት፣ በመተንተን እና ተግባራዊ በማድረግ ውስጥ ኅብረቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ በበኩላቸው መንግሥት ሰላምን ለማስፈን እየሠራቸው የሚገኙ ሥራዎች መሬት ላይ መውረድ እና ተግባራዊ መሆን የሃይማኖት አባቶች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው ያሉ ሲሆን፣ የተጀመሩ የሰላም ሂደቶች የተሳኩ እንዲሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሓላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
በምሥረታ ጉባኤው ላይ ለኅብረቱ መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ለጀስቲስ ፎር ኦል እውቅና ተሰጥቷል፡፡ የኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ኅብረቱን የሚመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትም በመድረኩ ተመርጠዋል፡፡ (ምንጭ:-የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን)

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts