Timran

በሰላም ግንባታ ውስጥ ትርጉም ያለው የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንዲቻል የተዘጋጀ የስትራቴጂ ቅየሳ መድረክ ተካሄደ

በሰላም ግንባታ ውስጥ ትርጉም ያለው የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንዲቻል የተዘጋጀ የስትራቴጂ ቅየሳ መድረክ በትምራን አዘጋጅነት ሠኔ 02 ቀን 2015 ዓ.ም በማግኖሊያ ሆቴል ተካሄደ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከየክልሉ ተወክለው ለተገኙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችኹ መልእክት አስተላልፈዋል።

መድረኩ ትምራን በየክልሉ ከሚገኙ ሴቶች ጋር ያካሄደቻቸው የሰላም ምክክሮች ማጠቃለያ መኾኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ማኅበራት፣ የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አባል የኾኑ የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የተወከሉ ሴቶች ተሳታፊ መኾናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችል ማኒፌስቶ ከመድረኩ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

የመድረኩን መከፈት ተከትሎ ኢትዮ ቲንክ ታንክ የተሰኘ አማካሪ ተቋም ባልደረቦች የኾኑት ነጸብራቅ ታመነ እና ኢዮብ አስፋው ስለ ሰላም ምንነት እና ማኒፌስቶ ጋር የተያያዙ ሐሳቦች ገለጻ አቅርበዋል። ተሳታፊዎችም ሐሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል።

በመቀጠል የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪዋ ማኅደር ዳዲ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች በተካሄዱ የሴቶች የሰላም ውይይቶች ከተነሡ ሐሳቦች የተጠናቀረ ረቂቅ የሰላም ማኒፌስቶ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።

ይኽንን መነሻ በማድረግ ተሳታፊዎች በአምስት ቡድን ተመድበው የየራሳቸውን ማኒፌስቶ አርቅቀው ገለጻ አድርገዋል። ከዚያም ተሳታፊዎች ከየምድቡ በቀረቡት ማኒፌስቶዎች ላይ ተጨማሪ ሐሳቦች አንሸራሽረዋል።

በመድረኩ ላይ ማጠቃለያ ሐሳብ የሰጡት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሰሎሞን ሴቶች የሰላም መሪ እንዲኾኑ ለማስቻል የወንዶች አጋርነት መኖር፣ የሕግ ማሻሻያ እና አፈጻጸም ችግሮች መቀረፍ፣ ሴቷን ማስተማር እና ማብቃት፣ ለሴቷ መዋቅራዊ ድጋፍ የሚደረግባቸውን መንገዶች ማፈላለግ፣ የክትትል እና ግምገማ አሠራር እንዲኖር ማድረግ፣ ለጾታ አካታችነት ሥራዎች በጀት መመደብ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሊካተቱ ይገባል በማለት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የሴቶች የሰላም ማኒፌስቶ ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደሚቀርብ እና ወደ ተግባር እንዲገባ የውትወታ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፤ ተሳታፊዎች ለነበራቸው ንቁ ተሳትፎም አመስግነዋል።

በስትራቴጂ ቅየሳ መድረኩ ላይ ቁጥራቸው ከ30 በላይ የኾኑ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts