Timran

በትምራን አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት ለአራት ቀናት የተሰጠው ሥልጠና ተጠናቀቀ

በትምራን አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 01 ቀን 2015 ዓ.ም ለአራት ቀናት በፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው የፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ሥልጠና ተጠናቀቀ።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን ተሳታፊዎች ከሥልጠናው መሠረታዊ ነገር ጨብጠዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ወደ የፓርቲዎቻቸው ሲመለሱም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሠሩ መክረዋል።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትምራን ቦርድ ሰብሳቢ መስከረም ገስጥ በአዚማን ሆቴል የተዘጋጀውን የስጦታ ኬክ ቆርሰዋል፤ ለሠልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወቀረት ሰጥተዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋ በዚሁ ወቅት ለሠልጣኞች ባስላለፉት መልእክት ትምራን ምርጫ ሲደርስ ከሚደረግ ሴቶችን የማንቃት እና የማስተማር የድግግሞሽ ተግባር ባሻገር በተደራጀ እና ትርጉም ባለው መልኩ ሴቶች በፖለቲካ እና በአመራርነት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የተቋቋመች መሆኗን ተናግረዋል። በዚህም እንቅስቃሴ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሴት ፖለቲከኞችን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት መቻሏን ጠቁመዋል።

ሆኖም ግን አሁንም ድረስ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሴቶች ተሳትፎ እዚህ ግባ የማይባልባቸው ሁኔታዎች በተጨባጭ እየታዩ መሆኑን አመልክተዋል።

ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አሁንም ድረስ ውስን መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ይህንን ለመለወጥ በየተወከልንበት ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ብዙ መሥራት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል። 

ትምራን የተቋቋመችበት ሌላኛው ዓላማ ሴቶች ሰላምን በማስፈን ረገድ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ መሆኑን የገለጡት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ በሀገራችን ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሴቶች ዋነኛ የችግሩ ተጋላጭ መሆናቸውን አውስተዋል። ስለሆነም በየቦታው የሚፈጠሩ መሰል ግጭቶችን ሴቶች በተፈጥሮ በተሰጣቸው የብልሃት ችሮታ በማብረድ ሰላም እንዲመጣ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ባለፉት አራት ቀናት በፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎት ሥልጠና በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፣ በሥልጠናው ላይ የተሳተፉ ሴት ፖለቲከኞች ወደየፓርቲያቸው ሲመለሱ ለአጋሮቻቸው ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ የየፓርቲያቸው ሴት ፖለቲከኞች ወደ አመራርነት በመስጠት እንዲመጡ በማገዝ እና ልዩ፣ ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።

ትምራን በቀጣይም የሴት ፖለቲከኞችን አቅም ለመገንባት ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርፃ መሥራት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት የተዘጋጀው የፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክሂሎትሥልጠና ከሲቪክ ማኅበራት ድጋፍ ፕሮግራም 2 በተገኘ የገንዘብ እገዛ የተካሄደ ነው።

ትምራን አቅማቸው የተገነባ እና በፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ያላቸው ሴቶች የመፍጠር ራእይ አንግባ የምትሠራ ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ስትሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ሴቶች ያላቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና በመስጠት ትልቅ ሥራ እያከናወነች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ከሴቶች ጋር ተያያዥ ተግባራት የሚያከናውኑ ከ50 በላይ የሲቪክ ማኅበራት ያቀፈው የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሴክሬታሪያት በመሆን እያገለገለችም ትገኛለች።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts