Skip to content

በትምራን አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሴቶች የሰላም መድረክ ተጠናቀቀ

በትምራን አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት የካቲት 09 እና 10 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደው የሴቶች የሰላም መድረክ ተጠናቅቋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በአሠልጣኞች በኩል በቀረቡ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና  ወስደዋል፤ የቡድን ውይይት ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል።

የሰላም ምንነት፣ የሰላም ዓይቶች፣ በደ/ብ/ብ/ሕዝቦች ክልል ሴቶች በሰላም ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ የማይችሉባቸው ጉዳዮች፣ ሴቶች እና የሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ምንነት፣ ሴትነት እና ሰላም ያላቸው ትስስር የሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በሥልጠናው ላይ ተነሥተዋል።

በዚሁ መሠረት በደ/ብ/ብ/ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በሰላም ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉ ከሚያግዷቸው ጉዳዮች መካከል የባሕል ተፅዕኖ መኖር፣ የአመለካከት ችግር፣ መብትን አለመጠየቅ እንዲሁም አለመጠቀም የሚሉት በተሳታፊዎች በኩል ተነሥተዋል። ሆኖም ሴቶች ወደ አመራርነት ለመምጣት መብታቸውን መጠየቅ እና ለሰላም መስፈን የአመራርነቱን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

በክልሉ ውስጥ ሰላም ለመገንባት እየተከናወኑ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሴቶችን ሚና አስመልክቶ ተሳታፊዎች የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ስለ ሰላም ውይይት እንደሚደረግ እና ሥልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በክልሉ ውስጥ ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማጎልበት አዳዲስ ሂደቶች፣ ተቋማት እንዲሁም  ሀብት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ተዋናይ እንዲሆኑ የብሔር ብሔረሰቦች የሽምግልና ሥርዓት በዘመናዊ መልኩ ለመጠቀም በሕግ ውስጥ እንዲካተቱ ቢደረግ ውጤት እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።

ለአብነት የጋሞ ብሔረሰብ የእርቅ እና የሰላም ዘዴ ቢስፋፋ፣ በጌዲኦ ሕዝብ ዘንድ ጠብ ሲፈጠር ሴቶች ደጅ ወጥተው ጉልበታቸውን ይዘው ሲጮኹ ማንም ሰው ሴቶችን አልፎ ለጠብ የማይጋበዝበት ልማድ ቢጠናከር፣ መንግሥት ችግር ሲያጋጥመው ብቻ ሴቶችን ስለ ሰላም ስበኩ ከማለት በዘለለ በአሠራር ሥርዓቱ ውስጥ አስገብቶ ተሳታፊ ቢያደርግ፣ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር ወደ ታች ወርዶ የክልሉን ሴቶች የሚያሳተፍ ስልት ቢቀይስ እና በመንግሥት በኩል ፖሊሲ ሲቀረፅ ሴቶች እንዲካተቱ ቢደረግ ብሎም ክልሉ የሰላም ፖሊሲ ቢኖረው የሚሉ ሐሳቦችን ተሳታፊዎች አንሥተዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ክልሉ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኑ ከየአካባቢው ከመጡ ሴቶች ልዩ፣ ልዩ ግብአት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን የሀዋሳ የሴቶች የሰላም መድረክ ንቁ ተሳትፎ የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሴቶች ለሰላም በቀዳሚነት ዘብ በመቆም ለሌሎች አርአያ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።      

አያይዘውም በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበሩ የክልል እና የዞን  ሴት አመራሮች ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ የነበራቸውን አስተዋጽኦ በመጨመር የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

ከተሳታፊዎች የተገኘው ግብአት ሀገራዊ የሰላም ስትራቴጂ ለመቅረጽ እና ለአመራሮች ግብአት እንዲሆን እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ሥልጠናው የተሳካ እንዲሆን የማስተባበሩን ድርሻ ለተወጣው የደቡብ ክልል ሴቶች ማኅበር እና የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲያ ጀማል እንዲሁም በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

ትምራን ሴቶች በፖለቲካዊ እና በማንኛውም ሕዝባዊ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ውሳኔ ሰጪ የሆኑባት አትዮጵያን ማየት የሚል ራእይ አንግባ የምትንቀሳቀስ ሕጋዊ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር ነች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *