Timran

ትምራን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ያዘጋጀችው የሁለት ቀናት የአመራርነት ሥልጠና ተጠናቀቀ

ትምራን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ጾታ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከጥቅምት 09-10 ቀን 2016 ዓ.ም ለ40 ሴት ተማሪዎች እና 10 የተመረጡ ወንዶች ለሁለት ቀናት ያዘጋጀችው የአመራርነት ሥልጠና ተጠናቀቀ።

በሁለት ቀናት ቆይታ ውስጥ አሠልጣኝ የነበሩት በፕላን ኢንተርናሽናል የወጣቶች ማብቃት መርሐ ግብር ውስጥ ሲሠሩ የቆዩት ወ/ሮ የሺእመቤት ዓለሙ፣ የአመለካከት ለውጥ ምንነት እና አስፈላጊነት፣ የሌሎችን ስሜት እና እይታ መረዳት፣ ራስን ለማዳመጥ መመሰጥ፣ የተግባቦት ምንነት፣ ዓይነቶች እና ጉድለቶች፣ በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ጉዳዮች ምንነት እና የግል የሕይወት ተሞክሮ፣ የቡድን ሥራ ምንነት እና አስፈላጊነት የሚሉ ርእሶችን በማንሣት በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ተግባር ተኮር ሥልጠና ሰጥተዋል።

በሁለተኛ ቀን የሥልጠና ውሎ ተማሪዎች ተጨባጭ ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማድረግ የሥራ እና ክሂሎት ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ ነቢሀ መሐመድ እንዲሁም የኢሕአፓ ዋና ጸሐፊ እና የሴት ፖለቲከኞች ጥምረት ጸሐፊ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን በሥልጠናው ላይ ተገኝተው የሕይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በዚኹ ወቅት ወ/ሮ ነቢሀ በወረዳ አመራርነት ወቅት የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ረገድ በነበሩበት አላባ ዞን ውስጥ እስከ ገጠር ድረስ በመውረድ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸዋል። አክለውም ሴትነት ጋር ተያይዞ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ወደ ውሳኔ ሰጭነት ለመምጣት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ በመኾኑ የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አባል በመኾን፣ በዚኽ ተሳትፎአቸው ከወረዳ አመራርነት በቀጥታ ወደ ፌዴራል ሥልጣን መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ወ/ሮ ደስታ በበኩላቸው በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ማደጋቸውንና እናታቸው የልጆችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርጉት የኑሮ ማብቃቃት ችሎታ በሕይወታቸው ላይ ትልቅ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
አያይዘውም እንኳን ለሴት ልጅ ለወንዶች ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቁ በሚባልባት ሀገር ውስጥ ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ የመጡበትን ኹኔታ ሲገልጹ፣ በቤታቸው ውስጥ ወንዶች ልጆች ባይኖሩም አባታቸው ፖለቲከኛ እና ጋዜጠኛ ስለነበሩ ዝንባሌ እንዳላቸው ተረድተው ማኅበራዊ ሳይንስ እንዲያጠኑ ቢፈልጉም ወደ ሕክምናው አድልተው ወደዚያ መስክ መግባታቸውንና የአባታቸውን ድንገተኛ እረፍት ተከትሎ ግን ሴት በመኾኔ ጫና ቢኖርም የአባቴን ራእዩን ማሳካት እችላለኹ በሚል ቁርጥ ውሳኔ ከሦስት ዓመታት በፊት የኢሕአፓ አባል በመኾን በአጭር ጊዜ በርካታ ሓላፊነቶች መሸከም መቻላቸውን አመልክተዋል።
ወሮ ደስታ በተሰማሩበት የሕክምና ሞያ የፖሊሲ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚታገሉ ገልጸው፣ ሴት ወጣቶች ወደ ውሳኔ ሰጭነት ለመምጣት የግድ የፖለቲካ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአአዩ የሥነ ባሕርይ ኮሌጅ፣ የሥነ ልቦና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የዩኒቨሲቲው የሥርዓተ ጾታ ዳይሬክቶሬት የበላይ ሓላፊ ዶ/ር ሰዋለም ጸጋ በበኩላቸው፣ በተለይ ሴት ወጣቶች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው የራስ መተማመን በማዳበር በየዝንባሌቸው መሠረት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ ሐሳብ የሰጡት ተማሪ ሠልጣኞች በጭብጥ ደረጃ የሚያውቋቸውን ጉዳዮች በሕይወታቸው ላይ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለአሠልጣኛቸው፣ ሥልጠናውን ላዘጋጁት ለአአዩ ሥርዓተ ጾታ ዳይሬክቶሬት እና ትምራን እንዲኹም አስተባባሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ፣ ሥልጠናውን የተከታተሉት ሴቶች እና የተመረጡ ወንዶች መሪ በመኾን ስለ ሴቶች ጉዳይ ሊናገሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፤ የተጣለባቸውን ሓላፊነት እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አክለውም በአሠልጣኝነት፣ በአስተባባሪነት እና በሠልጣኝነት ለተሳተፉ ኹሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ትምራን ያዘጋጀችው ይኽ የወጣቶች አመራርነት ሥልጠና ከፍሪደም ሐውስ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበሩት ተማሪዎች የአመራርነት ሥልጠና መውሰዳቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts