Timran

ትምራን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የአመራርነት ሥልጠና መስጠት ጀመረች

ትምራን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ (6 ኪሎ ግቢ) የተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሚያጠኑ 40 ሴት ወጣቶች እና የተመረጡ 10 ወንድ ተማሪዎች ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአመራርነት ሥልጠና መስጠት ጀመረች።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የትምራን ጊዜአዊ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ማኅደር ዳዲ፣ ትምራን የሴቶችን የፖለቲካ እና ሕዝብ አስተዳደር ዘርፍ ለሚኖራቸው ተሳትፎ ለማሳደግ ከሦስት ዓመታት በፊት የተመሠረተች ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር መኾኗን ገልጸዋል። ይኽንን ዓላማ በማንገብም ላለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ስትሠራ የቆየች ሲኾን፣ በተለይም ደግሞ ወጣት መሪዎችን ከማፍራት አንፃር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ስትሠራ መቆየቷን ጠቅሰዋል።

ወጣቶች ሀገር ተረካቢዎች እንደ መኾናቸው መጠን በኹሉም የሕይወት መስክ የአመራርነት ክሂሎት ያስፈልጋቸዋል ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ ይኽንንም እውን ለማድረግ ትምራን ፕሮጀክት ቀርፃ በዋናነት ሴት ወጣቶች ከታች ጀምሮ እየበቁ እንዲመጡ ለማድረግ እየሠራች መኾኑን ተናግረዋል።

ይኽንን ዓላማ እውን ለማድረግ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሚገኙ ወጣቶች ቀደም ሲል ለሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የአመራርነት ሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መድረክ አዘጋጅታ እንደነበር ገልጸው፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተዘጋጀው ይኽ ሥልጠና ኹለተኛው መድረክ መኾኑን አመልክተዋል። አያይዘውም ትምራን ሴቷ ሰላምን ትምራ የሚል ፕሮጀክት በመቅረፅ በተለያዩ ክልሎች የሴቶች የሰላም የእግር ጉዞዎች እና የሴቶች የሰላም መድረኮች ማዘጋጀቷን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ዳይሬክተር ማተቤ ታረቀኝ ሥልጠናውን በክብር እንግድነት የከፈቱ ሲኾን፣ ሴቶች ራሳቸውን በማብቃት ወደ መሪነት ለመምጣት ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል፤ በትምራን የተዘጋጀውን የአመራርነት ሥልጠና በንቃት እንዲከታተሉም አሳስበዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts