Timran

ትምራን ሴቶች ለሰላም ግንባታ እና ውትወታ በሚል ጭብጥ ለመካከለኛ አመራር ሴቶች ሥልጠና መስጠት ጀመረች

ትምራን ሴቶች ለሰላም ግንባታ እና ውትወታ በሚል ጭብጥ ለመካከለኛ አመራር ሴቶች ያዘጋጀችው ለሦስት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተጀመረ።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ትምራን ሴቶች ወደ ፖለቲካ አመራር እና ውሳኔ ሰጭነት እንዲመጡ የማስቻል ራእይ ሰንቃ ከአራት ዓመታት በፊት የተመሠረተች ነች ብለዋል። ባለፉት ጊዜያት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ሴቶች የአመራርነት ሥልጠናን ጨምሮ ሴቷ ሰላምን ትምራ በሚል ፕሮዤ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ሴቶች የአቅም ግንባታ እና ውትወታ ተግባራት ማከናወኗን ገልጸዋል።

ከክልሎች የተገኙ ግብአቶችን መነሻ በማድረግ ከሰላም ግንባታ ጋር በተያያዘ የመካከለኛ አመራር ሴቶች ጥምረት ምሥረታ ማከናወኗን፣ ጥምረቱ ሲመሠረት ከተገኙ ግብአቶች አንዱ የሰላም ግንባታ ሚና እና ውትወታ ላይ ሥልጠና በመኾኑ ይኽ መድረክ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። ከዚኹ ጎን ለጎን በከፍተኛ እና ዝቅተኛ አመራር ደረጃ የሚገኙ ሴቶች ለሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል ጥምረት ለመመሥረት ጥረት በማድረግ ላይ መኾኗን ጠቅሰዋል።

ሥልጠናውን በመስጠት ላይ የሚገኙት አስተዋይ ሳሙኤል የሰላም ምንነት እና አስፈላጊነት ላይ የመወያያ ሐሳብ አቅርበው ሠልጣኞች የራሳቸውን ምልከታ አቅርበዋል።

ሰላም ሲነሣ የግጭት ምንነት የማይቀር በመኾኑ ብያኔው በተመለከተ ግጭት ሴቶችንና ወንዶችን በተለየ መልኩ የሚጎዳ ነው ብለዋል፤ ይኽም በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያሉ ፍላጎቶች እና ምላሾች የሚለያዩ በመኾናቸው የተነሣ እንደመጣ ገልጸዋል።

ሴቶች ግጭት ሊያባብሱ የሚችሉባቸው ኹኔታዎች ቢኖሩም፣ የሰላም አምባሳደሮች መኾናቸው ግን የታወቀ ነው ብለዋል።

በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ሴቶች ከወንዶች የተሻሉ ናቸው ያሉት አሠልጣኟ፣ ይኽም ማኅበረሰቡ ውስጥ ነዋሪ በመኾናቸው የችግሮችን ምንጭ በተሻለ የማወቅ እድል ያላቸው ብሎም ባሕሎችና ወጎች አክብረው የሚኖሩ በመኾኑ የመጣ ነው ብለዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts