Timran

“ትምራን-ሴቶች በሰላም አመራርነት ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚል ጭብጥ የተካሄደው የሥዕል ዐውደ ርእይ መድረክ ተጠናቀቀ

“ትምራን-ሴቶች በሰላም አመራርነት ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚል ጭብጥ ከታኅሣሥ 01-02 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል የተካሄደው የሥዕል ዐውደ ርእይ መድረክ ተጠናቀቀ።

ለሁለት ቀናት የቆየውን የሥዕል ዐውደ ርእይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጎበኙት ሲኾን፣ ተጋባዥ አምባሳደሮች፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ተወካዮች፣ የሲቪክ ማኅበራት አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ጎብኝተውታል። ከዐውደ ርእዩ ጎን ለጎን ሴቶች በሰላም አመራርነት ውስጥ ያላቸው ሚናን በተመለከተ የምክክር መድረክ ተከናውኗል።

የሁለተኛው ቀን የውይይት መድረክ የከፈቱት የትምራን ጊዜአዊ ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ መድረኩን በእንኳን ደኅና መጣችኹ የከፈቱት ሲኾን፣ በመቀጠል ሴቶች በሰላም አመራርነት ውስጥ ያላቸው ሚና ምን መኾን አለበት በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል። ይኽንን ተከትሎ በመድረኩ ላይ ከተገኙት ተጋባዥ እንግዶች መካከል በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ፣ ያለ ፖለቲካ ተሳትፎ ሴቶች ሥልጣንም ኾነ የውሳኔ ሰጭነት አቅም ሊኖረን ብሎም ውሳኔዎችንም ልናስቀይር አንችልም፤ ስለኾነም አስተዋጽዎአችን ምንድነው ብለን መጠየቅ አለብን የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በጤና ዙሪያ ላይ የሚሠራው እና መንግሥታዊ ድርጅት ያልኾነው ኢንጀንደር ሄልዝ ባልደረባ የኾኑት የሕግ ባለሞያዋ ሜሮን አርጋው በበኩላቸው፣ ሴቶች ለመብቶቻችን ለመታገል አንድነት ሊኖረን ይገባል። በግጭቶች እና ጦርነቶች የተነሣ በቀዳሚነት ተጠቂዎች ሴቶች ነን፤ ስለዚኽ ሴቶች ግጭቶች እንዲቆሙ በኅብረት መጠየቅ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ተርካንፌ ለዘላቂ ልማት የተሰኘ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር ሰብሳቢ የኾኑት ወርቅነሽ ቤጊ ደግሞ፣ በሴቶች የሰላም አመራርነት ላይ የሚከናወኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ሴቶች በጉዳዩ ላይ ያለንን ባለቤትነት መጨመር፣ ተባብሮ መሥራት እና ተጨባጭ የሴቶችን ውክልና ማሳደግ ላይ ውጤት አምጥተናል ወይ የሚሉ ጉዳዮችን በአንክሮ መገምገም አለብን ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሴቶች ማኅበር ሰብሳቢ ሃይማኖት ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ሴቶች በሰላም ጉዳይ ላይ ያላቸውን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፤ በሰላም ዙሪያ የሚሠሩ ሴቶችን ማድነቅ እና መደገፍ አለብን፤ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በየደረጃው አስገዳጅ ሕጎች ሊተገበሩ ይገባል ሲሉ ጠቁዋል።

ስብስብ ለሰብአዊ መብቶችን በሓላፊነት የሚመሩት መሱድ ገበየሁ እንዲኹ፣ በሰላም ጉዳይ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ አስፈላጊነት አንሥተው፣ ነገር ግን የሲቪክ ማኅበራት በሀገሪቱ የሰላም እና ደኅንነት ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ አስተያየት ለመስጠት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ ዝቅተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል። ስለኾነም ሴቶች በሰላም አመራርነት ውስጥ በያገባኛል መርህ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሰላም አመራርነት ውስጥ ሴቶች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው በሓላፊነት ስሜት ወደፊት ለመምጣት ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ተሳታፊዎች ዐውደ ርእዩን የጎበኙ ሲኾን፣ ጎን ለጎን የእርስ በርስ ትውውቅ እና የሐሳብ ልውውጥ አድርገዋል።

ለሁለት ቀናት የቆየው የሥዕል ዐውደ ርእይ በጀርመንን ዓለም አቀፍ ትብብር፣ ሲቪል ፒስ ፕሮሰስ ዘንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ትምራን ከኢትዮጵያ ሴት ሠዓሊያን ማኅበር እና በወጣቶች አቅም ግንባታ ላይ የሚሠራ ሪዲም ዘጀኔሬሽን ከተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው ሲኾን፣ 8 ፕሮፌሽናል እና 5 አማተር ሴት ሠዓሊያን ከ30 በላይ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts