Timran

ትምራን በተለያዩ ውትወታ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ስታከብር የቆየችውን የአራተኛ ዓመት ክብረ በዓል አጠናቀቀች

ትምራን ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ እና በሀገሪቱ ውሳኔ ሰጭነት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው የማስቻል ራእይ በመሰነቅ መጋቢት 2012 ዓ.ም ከኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን የምዝገባ ምስክር ወረቀት በማግኘት ሥራ ከጀመረች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።

መጋቢት ዓለም አቀፍ የሴቶች ወር እንደመኾኑ መጠን ትምራን የተለያዩ የውትወታ እና የአቅም ግንባታ ተግባራት በማከናወን አራተኛ ዓመት ክብረ በዓሏን ስታከብር ቆይታለች።

የትምራን መሥራቾች፣ የቦርድ አባላት፣ ባለድርሻ አካላት፣ ተባባሪዎች እና ለጋሾች እንኳን ለትምራን አራተኛ ዓመት ምሥረታ አደረሳችኹ።

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ትምራን ባስቀመጠቻቸው የውትወታ፣ ጥናት እና ምርምር፣ ጥበቃ እና ከለላ፣ አቅም ግንባታ እንዲኹም ትስስር እና አጋርነት በተሰኙ አምስት ምሰሶዎች መሠረት ከበርካታ ሀገር በቀል እና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን አከናውናለች።

ትምራን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በምርጫ ጊዜ ለሴት ፖለቲከኞች የሚኖሩ መልካም አጋጣሚዎች እና ተግዳሮቶች ላይ የውይይት መድረክ የማዘጋጀት፣ ለሴት ተመራጭ እጩዎች አቅም ግንባታ ሥልጠና የመስጠት እና በምርጫ ታዛቢነት የመሳተፍ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲቋቋም ለኮሚሽነርነት ሴት እጩዎችን የማቅረብ፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ተግዳሮቶች እና እድሎች ላይ ምክክር የማድረግ፣ ለሴት ሚዲያ ባለሞያዎች ለሥርዓተ ጾታ ትኩረት የሚስቡ ዘገባዎችን የማቅረብ እንዲኹም ለሐዋሳ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የአመራርነት ሥልጠና የመስጠት ሥራዎች ሠርታለች።

በስምንት ክልሎች የሴቶችን የሰላም ግንባታ ሚና ለማሳደግ ያለሙ መድረኮች እና የሰላም የእግር ጉዞዎች አዘጋጅታለች፤ በአገራዊ የሰላም ስትራቴጂ ላይ ከፌዴራል ሥራ አስፈጻሚ ሴት አመራሮች ጋር ምክክር አድርጋለች፤ ለሴት ፖለቲከኞች የአመራርነት፣ በፖለቲካ ውስጥ የተግባቦት ክሂሎት እና ምርጫ ቅስቀሳ ሥልጠና ሰጥታለች፤ በፖለቲካ ውስጥ በጾታ ላይ የተመሠረተ ጥቃት የተመለከተ ሥልጠና ለወንድ ፖለቲከኞች አዘጋጅታለች።

በሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ሥርዓቶች ላይ የሴቶች ሚና፣ በፌዴራል እና በክልል የመንግሥት የሕግ አውጭ እና አስፈጻሚ አካላት ውስጥ የሴቶች ውክልና ኹኔታ፣ በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ የሴት ዳኞች ውክልና፣ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ብሎም በሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ዘዴዎች የሴቶች ሚና የሚሉ ጥናቶችን አዘጋጅታ ለኅትመት አብቅታለች።

ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኞች መብቶች እና አካታችነት ላይ ያተኮረ ሥልጠና በመስጠት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የሲቪክ ማኅበራት ብሔራዊ የጥናት ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ፣ በትውልዶች መካከል ለሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ምክረ ሐሳብ ማፍለቂያ መድረክ በማዘጋጀት፣ ሴቶች በሰላም አመራር ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማሳየት ያለመ ትምራን የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርእይ አዘጋጅቶ በማሳየት፣ በ4ኛው የአፍሪካውያን ሴት ከፍተኛ አመራሮች የሰላም እና ደኅንነት ሚና ውይይት ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ አድርጋለች።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የልምድ ልውውጥ በማካሄድ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ መሥራች አባል በመኾን ላለፉት ኹለት ዓመታት በጽ/ቤትነት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኹለት ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በዘጠኝ ክልሎች የሴቶችን አጀንዳዎችን ለመለየት የሚያስችሉ 4000 በላይ ሴቶች የተሳተፉባቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረኮችን አዘጋጅታለች። ከየመድረኮቹ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማጠናቀር ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቅረብ ሂደት ላይ ትገኛለች።

እስካኹን የተከናወኑት ተግባራት ትምራን ሴቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተገቢ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማስቻል የሰነቀችውን ራእይ እውን ለማድረግ አበረታች ናቸው።

በዚኹ አጋጣሚ ለትምራን ሥራዎች እገዛ በማድረግ አብረውን ሲሠሩ ለቆዩት የኖርዌይ ክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ኦፕን ሶሳይቲ፣ ዩኤስኤይድ/ኤንዲአይ፣ ኦቲአይ፣ ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ እና አይአርአይ፣ የብሪታኒያ መንግሥት ሲቪል ሳፖርት ፕሮግራም 1 እና 2፣ ፕላን ኢንተርናሽናል፣ አይሪሽ ኤይድ፣ ፍሪደም ሐውስ፣ ዩኤን ዉመን፣ ፍሬደሪክ ኤበርት ስቲፍተንግ፣ የጀርመን ኤምባሲ፣ የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር የሲቪል ፒስ ሰርቪስ፣ ሲሃ፣ ኢንክሉሲቭ ፒስ እና የካናዳ ኤምባሲ ምስጋና ታቀርባለች።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts