Timran

ትምራን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ከሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር አከበረች

ትምራን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ከሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም በአዚማን ሆቴል አከበረች።

የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢሩሳሌም ሶሎሞን በበዓሉ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በሥልጠና ላይ ለሚገኙት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ሴት አባላት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

በዓሉ ዲጂታል ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ለጾታ እኩልነት በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጇ፣ ሴቶች ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ የሚላቸው ወቅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይም ሴት ፖለቲከኞች የድምፅ አልባ ሴቶች ወኪል በመሆናቸው ቴክሎጂ በመጠቀም ረገድ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው እና በሥልጣን እርከን ላይ ሲገኙ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች አርአያ በመሆን ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የትምራን ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ብሌን አሥራት በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ለሚገኙ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ ጥምረት አባላት እንኳን ለዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

በዓሉ በኢትዮጵያ ለ47ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ112ኛ ጊዜ የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓል አከባበር መነሻው የአውሮፓውያን ሴቶች የእኩልነት ጥያቄ እንደነበር፣ በዓሉም በጀርመን ሀገር መከበር እንደጀመረ ተናግረዋል።

የሴቶች ቀን በተለየ መልኩ የሚከበረው ጠንካራ ሴቶችን ለማወደስ፣ የደረስንበትን የእድገት ደረጃ ለማየት እና እንዴት እንደመጣን ለመገምገም ነው ያሉት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ በኢትዮጵያ አርአያ የሚሆኑ በርካታ ሴቶች መኖራቸውንና ዕለቱ ልምድ የምንቀስምበት ነው ብለዋል።

አያይዘውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖች ለማሳየት ያህል ዕድሜአቸው ከ15-44 ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ከጦርነት፣ ከተሽከርካሪ አደጋ፣ ከካንሰር እና ሌሎች ጉዳዮች የበለጠ አስገድዶ መደፈር እንደሚያሳስባቸው፣ ባለንበት ወቅት 603 ሚሊየን ሴቶች ጾታዊ ጥቃት እንደ ወንጀል የማይቆጠርባቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

በሀገራችን ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከሕግ ማእቀፎች መደንገግ እና የመብት ተሟጋቾች መጨመር ጋር ተያይዞ በሴቶች መብት መከበር ረገድ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አሁንም በግጭት ውስጥ አስገድዶ መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬ 50 ዓመት በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ሴቶች አንድ ተወካይ ብቻ የነበራቸው ሲሆን፣ አሁን ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ሴቶች 30 በመቶ መቀመጫ መያዝ መቻላቸውን አመልክተዋል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዲጂታል ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ለጾታ እኩልነት በሚል ጭብጥ ሲከበር፣ ሴት ፖለቲከኞች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ትምራን ሴቶች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግሥት ሥልጣን እርከን ድረስ እንዲደርሱ በትኩረት መሥራት እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በዚህ ሳምንት የተዘጋጀው ሥልጠና ዋና ዓላማም ሴት ፖለቲከኞች በፖለቲካ ተግባቦት እና በምርጫ ዘመቻ ክሂሎት የላቁ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሴቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ እውን ለማድረግ በሴቶች እኩልነት ከሚያምኑ ወንድ አጋሮች ጋር በመሆን መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts