ትምራን የ2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ታዛቢ በተገኘበት መስከረም 05 ቀን 2016 ዓ.ም አካሄደች።
ጠቅላላ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የትምራን ቦርድ ሰብሳቢ መስከረም ገስጥ፣ ማኅበሯ ሴቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተገቢ የውሳኔ ሰጭነት ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል ከሦስት ዓመታት በፊት መቋቋሟን ገልጸዋል። ትምራን በአጭር ዓመታት ውስጥ ስኬታማ ጉዞ ማድረጓንም አመልክተዋል።
የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤውን የሚመሩ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ጸሐፊ ምርጫ እንዲኹም የአጀንዳ ማጽደቅ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመቀጠል የቦርድ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም፣ የ2015 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም፣ የሒሳብ ዘገባ እና የሒሳብ መርማሪ ዘገባዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዚኹ መሠረት ትምራን በዓመቱ ውስጥ የነበራት ጥቅል የሥራ አፈጻጸም 72 በመቶ መኾኑን ዘገባውን ያቀረቡት የትምራን ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ ተናግረዋል።
በፋይናንስ ረገድ ትምራን በዓመቱ ውስጥ ከሀገር ውስጥ እና ውጭ ምንጮች ካገኘችው ገንዘብ መካከል 96 በመቶው ለፕሮግራም ተግባራት ያዋለች ሲኾን፣ የቀረው 4 በመቶ ብቻ ለአስተዳደራዊ ወጪዎች መጠቀሟን የሒሳብ ዘገባዎች አሳይተዋል።
ትምራን የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክን በጽ/ቤትነት በማገልገል ላይ ስትኾን፣ የጥምረቱ ሥራዎች እንደ አንድ ፕሮጀክት ራሳቸውን ችለው እንዲከናወኑ በማድረግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቧም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ይኽንን ተከትሎ የትምራን የ2016 ዓ.ም እቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፤ ግብአትም ተሰጥቷል። ከዚያም ትምራን አኹን ከደረሰችበት እድገት ጋር እንዲመጣጠን ለማድረግ ከአምስት ዓመት የተከለሰ ስልታዊ እቅድ ውስጥ አዲስ ተቋማዊ መዋቅር ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፤ በተሰጡት ግብአቶች መሠረት ተስተካክሎ እንዲጸቅድም ተወስኗል።
በመጨረሻም ባለፈው ዓመት ትምራንን በቦርድ አባላት ሲያገለግሉ የነበሩ አባላትን ለመተካት ምርጫ የተካሄደ ሲኾን፣ ከነባሩ ሁለት እንዲኹም ሦስት አዳዲስ የቦርድ አባላት በጉባኤው ላይ ተመርጠዋል።
ለተሰናባች የቦርድ አባላት ደግሞ እውቅና የመስጠት መርሐ ግብር ተከናውኖ የጠቅላላ ጉባኤው መርሐ ግብር ተጠናቅቋል።