Timran

ትምራን ያዘጋጀችው በመንግሥት አመራርነት ላይ የሚገኙ ሴት መሪዎች የሰላም መድረክ ተካሄደ

በመንግሥት አመራርነት ላይ የሚገኙ ሴት መሪዎች የሰላም መድረክ እና ሴቶች በሰላም ግንባታ ውስጥ ያላቸው ስልታዊ ተሳትፎ የተመለከተ መድረክ በትምራን አዘጋጅነት በስካይላይት ሆቴል ሠኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሄደ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ቦርድ ሰብሳቢ መስከረም ገስጥ የሴቶች ተሳትፎ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው። ሴቶች በግል ሰብአዊ መብታቸውን መጠቀም ብሎም ለሌሎች መትረፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አያይዘውም ሴቶች በሰላም ጉዳይ መሳተፋቸው አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን ወሳኝ በመኾኑ መንግሥት ይኽንን መብታቸውን ሊያከብርላቸው ይገባል። ነገር ግን ባለፉት ጊዜያት ሴቶች በሰላም ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እዚኽ ግባ የሚባል አይደለም፤ የሀገሪቱን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የሚይዙ ሴቶች ፍላጎቶቻቸውንና ምኞቶቻቸውን እውን ለማድረግ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ትምራን ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሴቶች የሰላም ውይይቶችን ስታከናውን የቆየች ሲኾን፣ እነዚኽን ውይይቶች መነሻ በማድረግ በአመራር ላይ የሚገኙ ሴቶች ጥምረት መመሥረት አልያም ቅንጅት መፍጠር የሚለው ላይ ለማወያየት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ሴቶች የጉዳዩ ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል ሐሳቡን ማስረፅ ላይ ኹላችንም ልንንቀሳቀስ ይገባል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ መንግሥት የሴቶችን ሰላም እና ደኅንነት በተመለከተ የሕግ ማእቀፍ በመቅረፅ ሂደት ላይ በመኾኑ እኛ ደግሞ ተግባራዊነቱ ላይ መሳተፍ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪዋ ማኅደር ዳዲ ትምራን ባለፉት ጊዜያት አማራ ክልል ጎንደር፣ ኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ጋምቤላ ክልል ጋምቤላ፣ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ቤኒሻንጉል ክልል አሶሳ፣ ደቡብ ክልል ሐዋሳ፣ አፋር ክልል ሰመራ እንዲኹም አዲስ አበባ ላይ ስምንት የሴቶች የሰላም መድረኮች ማዘጋጀቷን ገልጸው፣ ከእነዚኽ አካባቢዎች የተገኙ ግብአቶችን መነሻ በማድረግ ከሴት አመራሮች ጋር መወያየት አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ በየክልሉ በተካሄዱት የሴቶች የሰላም መድረኮች ከተነሡ ጉዳዮች መካከል ለሰላም እጦት ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የመልካም አስተዳደር እጦት እና ሥራ አጥነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ የደኅንነት እና ፍትሕ ተቋማት አሠራር ችግሮች፣ የጎሳ ግጭት እና የተዛቡ ትርክቶች መኖር፣ የሃይማኖት አክራሪነት መጨመር፣ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን የምናስተናግድበት አቅም ዝቅተኛ መኾን፣ የግጭት አፈታት ስልቶቻችን ደካማ መኾን ችግሩ እንዲመላለስ ማድረጉ የሚሉትን በመድረኩ ላይ አቅርበዋል።

እነዚኽ ጉዳዮች በሴቶች ላይ ሞት እና ስቃይ፣ መፈናቀል እና ስደት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃቶች መበራከት ማስከተሉን ጠቅሰዋል።

በመቀጠል ከተሳታፊዎች ሐሳቦች እና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ተሳታፊዎች ትምራን ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማስቻል ለምታደርገው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ የሴቶች ኅብረት መመሥረት አስፈላጊ ስለመኾኑ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የማጠቃለያ ሐሳብ የሰጡት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ በመድረኩ ለተገኙ ሴት አመራሮች ሴቶች በሰላም ግንባታ መሳተፍ የሚችሉባቸውን ስልቶች መቀየስ እንዲችሉ በየሩብ ዓመቱ በመገናኘት እንዲሠሩ የሚያስችሉ መድረኮች እንደሚኖሩ በመግለጽ ለተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበው ውይይቱን ዘግተዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts