ትምራን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም ያዘጋጀችው በመካከለኛ ደረጃ አመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶች የሰላም ግንባታ ሚና የግማሽ ቀን የምክክር መድረክ የጋራ ኅብረት በመመሥረት ተጠናቀቀ።
የትምራን ቦርድ አባል ራቤል ደሳለኝ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችኹ መልእክት ያስተላለፉ ሲኾን፣ ትምራን ከሦስት ዓመታት በፊት የተመሠረተች የሴቶች የመሪነት ሚና እና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የምትሠራ ሀገር በቀል ሲቪክ ማኅበር ነች ብለዋል።
ከምሥረታዋ ማግስት በነበረው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የአቅም ግንባታ እና ውትወታ ተግባራት ማከናወኗን፣ ከዚያም በተከታታይ ዓመታት ውስጥ ሴቶች በሰላም ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ ለማድረግ ስትሠራ መቆየቷን ተናግረዋል።
በዋናነት በአራት ፕሮግራሞች ማለትም በጥናት እና ምርምር ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አስቻይ ሕጎች መኖር አለመኖራቸው ላይ በማተኮር በጥናት መለየት፣ በውትወታ ዘርፍ ሴቶች በኹሉም መስክ ተሳታፊ እንዲኾኑ ምቹ ኹኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ በአቅም ግንባታ ዘርፍ የሴቶች የመሪነት ሚና እንዲጠናከር እና ወጣት ሴት መሪዎች ወደፊት እንዲመጡ ማስቻል፣ ጥምረት በመፍጠር የሴቶችን ድምፅ ለማሰማት ንቅናቄ መፍጠር እንዲኹም የሀገራዊ ምክክር ሂደት፣ አተገባበር እና ውጤት በሴቶች እንዲመራ በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ሓላፊ ኂሩት ዴሌቦ ሰላም ለኹሉም ነገር መሠረት ነው መኾኑን ጠቅሰው፣ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የኹሉም ዜጋ አበርክቶ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ማብቃት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ በበኩላቸው፣ ሴቶችን ማብቃት ኅብረተሰብን ማብቃት መኾኑን ጠቁመው፣ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶች ሚና የማይተካ መኾኑን ገልጸዋል።
ትምራን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የምታከናውናቸው ተግባራት ለመደገፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ዝግጁ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ትምራን በስምንት የክልል ከተሞች ከ350 በላይ ከኾኑ ሴቶች ጋር በሰላም ጉዳይ ባደረገችው የሰላም ውይይት የተገኙ ግብአቶች ረቂቅ ሰነድ በሥራ አስኪያጇ ማኅደር ዳዲ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች፣ መንግሥት ተቋማት፣ ዴሞክራሲ ተቋማት (ምርጫ ቦርድ፣ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ)፣ ፋይናንስ ተቋማት፣ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት፣ ሞያ ማኅበራት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች (ኢትዮ ቴሌኮም)፣ ፀጥታ ተቋማት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ጋዜጠኞች፣ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች ጨምሮ 36 ገደማ ሴቶች ተገኝተው በርካታ ሐሳቦች አንሸራሽረው በቀጣይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ኅብረት መሥርተዋል።
ኅብረቱ በመካከለኛ አመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲኖራቸው የሚሠራ ይኾናል፡፡

የትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ በሲቪክ ማኅበራት ብሔራዊ የጥናት ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቀረቡ
የትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የሲቪክ