Timran

ከዘጠኝ ክልሎች የተሰባሰቡ የሴቶችን አጀንዳዎች አጠናቅሮ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቅረብ የተዘጋጀው የመክፈቻ ምክክር መድረክ ተጠናቀቀ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከሰባት ክልሎች እና ኹለት ከተማ አስተዳደሮች ያሰባሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች አጠናቅሮ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቅረብ ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ያካሄደው የመክፈቻ ምክክር መድረክ ተጠናቀቀ።

ለመድረኩ ተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችኹ መልእክት ያስተላለፉት የጥምረቱ ጽ/ቤት የኾነችው ትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ በአኹኑ ወቅት ከ56 በላይ አባል ድርጅቶችን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ጥምረት ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከኹለት ዓመት በፊት መቋቋሙን አውስተዋል።

ጥምረቱ ከመጋቢት 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ (መተከል እና አሶሳ ዞኖች) ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በጥቅሉ 46 መድረኮች በአይሪሽ ኤይድ #IRISH AID እና ዩኤስኤይድ/ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት #USAID/NDI ድጋፍ በማዘጋጀት የሴቶችን አጀንዳዎች ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

በዚኽ የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ከዘጠኝ ክልሎች የተሰባሰቡ አጀንዳዎች በጥምረቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ሥራ አሰባሳቢ ቡድን፣ በጥምረቱ ባለሞያዎች እና በሥነ ጾታ ዘርፍ ጥናት እና መረጃ ጥንቅር ልምድ ያለው አማካሪ የጋራ ርብርብ ተጠናቅረው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲሰጡ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ለመወያየት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በመቀጠል የጥምረቱ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ በተንቀሳቀሰባቸው ዘጠኝ ክልሎች የሴቶች አጀንዳ የተሰባሰበባቸው መንገዶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ይኽንን ተከትሎ ኢንክሉሲቭ ፒስ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተመራማሪ የኾኑት ፊሊፕ ፖፕለርሬውተር፣ ሳይንሳዊ አጀንዳ ማጠናቀር ሥነ ዘዴ እና አጀንዳዎችን ሥነ ጾታዊ ቅርፅ ማስያዝ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አቅርበዋል። በቀረበው ገለጻ ላይ ጥያቄዎች ተነሥተው ከተመራማሪው ምላሽ ተሰጥቷል።

ከዚያም በጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አማካኝነት ከዘጠኝ ክልሎች የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን አጠናቅሮ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስገባት የሚቻልበትን ሂደት ለማስተባበር የተቀጠረው አማካሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ በየነ፣ የአጀንዳ ጥንቅር ስልቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል።

የቀረበውን መነሻ ሐሳብ ተከትሎ በተሳታፊዎች በኩል ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲኾን፣ የአጀንዳ ማጠናቀር ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ በርካታ ግብአቶች ተገኝተዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር እና የጥምረቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የኾኑት ሳባ ገ/መድኅን፣ ጥምረቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸው ተግባራት ጉልህ መኾናቸውን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በተለይ የሴቶችን ድምፅ ማሰባሰብ መቻሉ በታሪክ የሚዘከር መኾኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የታሪክ ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ በሚል የሚቀርበው በዚኽ መልኩ በትንሽ፣ በትንሹ ተሠርቶ፣ በሰነድ ተቀምጦ ለሌሎች ተሞክሮ መኾን እንደቻለ ኹሉ ጥምረቱ ያከናወናቸው ተግባራት በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች ሀገራት ማስተማሪያ እንደሚኾን ርግጠኛ ነኝ፣ እንኳን ለዚኽ ቀን አደረሰን ብለዋል።

በምእራፍ ኹለት ጥምረቱ እስካኹን መድረስ ባልቻለባቸው አማራ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ እናማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ሴቶች አጀንዳዎች ተሰባስበው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚቀርቡበት መንገድ እንዲመቻች አሳስበው መድረኩን አጠቃልለዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts