Timran

ከጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አባላት የቀረበ የሰላም ጥሪ!

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ መጋቢት 2014 ዓ.ም ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል የተቋቋመ ሲኾን፣ በአኹኑ ወቅት ከ50 በላይ አባል ድርጅቶችን ይዞ ይንቀሳቀሳል።

እኛ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አባላት፣ ሴቶች እኩል የኅብረተሰብ ክፍል እንደ መሆናቸው መጠን በየትኛውም መልኩ በሚከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ከሚደርስባቸው ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ሊጠበቁ ይገባል ብለን እናምናለን። ከዚኽ ባሻገር ሴቶች ለመብታቸው መሟገት፣ ደኅንነታቸው መረጋገጥ እና በጦርነት ሲጎዱ መታገዝ ይገባቸዋል ብለን በጽኑ እናምናለን።
የትጥቅ ግጭቶች በሴቶች ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ እና ለድርብርብ ጥቃቶችም እንደሚያጋልጡ እንገነዘባለን። በዋናነት ሴቶች በአብዛኛው ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች ዒላማ ይሆናሉ፤ ይኽም የስቃይ፣ የፍትሕ እጦት አዙሪት እንዲቀጥል እና መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲጣስ ያደርጋል።

እንደ ሀገር ከቅርብ ጊዜ በፊት በትግራይ በተፈጠረው ግጭት ካጋጠመው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በአግባቡ ሳናገግም በአኹኑ ወቅት ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ እና የፀጥታ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አሳዛኝ ነው። በተጨማሪም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ግጭቶች በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም የሚታዩ ሲኾን፣ በእነዚኽ የሰላም መደፍረሶች ውስጥ ሴቶች ዋነኛ ተጠቂዎች መኾናቸው እሙን ነው። በመኾኑም እዚኽም፣ እዚያም የሚታዩት ችግሮች ወደተባባሰ ሀገራዊ ቀውስ ከመሸጋገራቸው በፊት በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ በአጽንኦት እንጠይቃለን።

ይኽንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጥምረቱ ከሚያቀርበው የሰላም ጥሪ በተጨማሪ የሚከተሉት ሐሳቦች በሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ እንዲተገበሩ እንጠይቃለን።

1. የሰብአዊ መብቶች መከበር፡- ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ በአጽንኦት እናሳስባለን።

2. ጥቃትን መከላከል እና የመብት ጥበቃ፡- ሴቶችን በትጥቅ ግጭቶች ወቅት ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት መከላከል እንደሚያስፈልግ አበክረን እንገልጻለን። ይኽም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎችንና ፖሊሲዎችን ማስፈጸም፣ ፍትሕ ማግኘትን ማረጋገጥ እንዲኹም የሕክምና፣ የሥነ ልቦና እና የሕግ ድጋፍን መስጠት ይጨምራል።

3. ማብቃት እና ተሳትፎ፡- በሁሉም የሰላም እና የፀጥታ ማስከበር ሂደቶች ላይ የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ እናበረታታለን። ከዚኽ ባሻገር ሴቶች ድምፃቸው እንዲሰማ፣ ሐሳባቸው በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ጎልቶ እንዲታይ፣ በማንኛውም ሰላማዊ ድርድሮች እና የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ በጎ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው እንጠይቃለን።

እኛ የጥምረቱ አባላት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሴቶችን መብት እና ደኅንነት እንዲጠበቅ የሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን እንዲኹም የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎች አጋር ድርጅቶች እና የተለያዩ አካላት ያወጡአቸውን የሰላም ጥሪዎች በመደገፍ የበኩላችንን ድርሻ እንደምንወጣ እናሳውቃለን። በዚኽ ሂደት ውስጥም በተቀናጀ መንገድ ሴቶች ከአደጋ የሚጠበቁበት፣ ለሁሉም ማኅበረሰብ ሰላማዊ ኑሮ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ አበክረን እንገልጻለን።

የሰላም ጥሪውን ያቀረቡ የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር አባል ድርጅቶች

• ሙጀጀጓ ሎካ የሴቶች ልማት ማኅበር-ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል
• ሮሺ ወዱ ፓስቶራል ውሜን ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን-አፋር ክልል
• ሲቄ የሴቶች ልማት ማኅበር
• ሲነርጂ ፎር ኮሙዩኒቲ ዴቨሎፕመንት-ድሬዳዋ
• ሳራ ፍትሕ ከሁሉም ሴቶች ማኅበር
• ሴታዊት ንቅናቄ
• ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ
• ሶማሌ ውሜን ዲያሎግ ስፔስ-ሶማሌ ክልል
• ሶማሌ ነን ስቴት አክተርስ ኮአሊሽን-ሶማሌ ክልል
• ራስ አገዝ የሴቶች ድርጅት
• ቁማን ውሜን ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን-ሶማሌ ክልል
• ተርካንፊ ለዘላቂ ልማት
• ትምራን
• ኒው ሚሌኒየም ውሜን ኢምፓወርመንት ኦርጋናይዜሽን
• አሶሴሽን ፎር ውሜንስ ሳንክቹዋሪ ኤንድ ዴቨሎፕመንት
• አድቮኬሲ ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት
• ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን
• ኢስት አፍሪካ ኢንሺየቲቭ ፎር ቼንጅ (I4C)
• ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ
• ኮንሰርን ፎር ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት
• ወጣት ሴቶች ሀገር አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት
• ውሜን ካን ዱ ኢት
• የሐረሪ ክልል ሴት አካል ጉዳተኞች ማኅበር
• የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች
• የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማእከል
• የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ማኅበር
• የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር
• የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር
• የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር (ኢ.ሕ.ባ.ሴ.ማ)
• የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማእከል
• የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት
• የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር
• የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ሴቶች ባለሞያዎች ማኅበር (ኢት.መ.ሴ.ባ.ማ)
• የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች (ኢሰመተ)
• የኢትዮጵያ ሠራተኛ መብቶች ተሟጋች
• የኦሮሚያ ክልል ሴቶች ማኅበር
• የአፋር ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን
• የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ማኅበር-ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ
• የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሴቶች ማኅበር-ደቡብ ክልል
• የድሬዳዋ መምህራን ማኅበር
• የድሬዳዋ ሴቶች ፌዴሬሽን
• የጋምቤላ ክልል ሴቶች ማኅበር
• ጋድ ፎር ፒፕል ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን
• ጣሊታ ራይዝ አፕ-ሲዳማ ክልል
• ፋሚሊ ሰርቪስ አሶሴሽን
• ፎረም ፎር አፍሪካን ውሜን ኢጁኬሽናሊስትስ
• ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ኢትዮጵያ

ነሐሴ 05 ቀን 2015 ዓ.ም

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts