በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር እና ትምራን አስተባባሪነት የተዘጋጀ የአካል ጉዳተኞች መብቶች እና አካታችነት ጭብጥ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሠኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በሳሬም ሆቴል ተሰጠ።
ሥልጠናውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና መንግሥታዊ አስተዳደር ጥናት ኮሌጅ መምህር የኾኑት ጠበቃ እና የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ዳኛቸው ቦጋለ ዋኬኔ (ዶ/ር) የአካል ጉዳተኞች መብቶችን እንደገና ማሰላሰል እና አካታችነት በሚል ጭብጥ ላይ አተኩረዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው ሥልጠናውን ሲጀምሩ በየአካባቢው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ኹኔታዎች መኖር አስፈላጊነት ላይ ሥዕላዊ ገለጻ ሰጥተዋል። በመቀጠል ለተሳታፊዎች ስለ አካል ጉዳተኝነት ያላቸውን ምልከታ የሚፈትሹ የሰዎች ብዝኀነት፣ የአካታችነት ተግባራት፣ የብዝኀነት እና አካታችነት እሴቶች፣ ባለድርሻ አካላት እና ሚና ጋር የተያያዙ ቅድመ ምዘና ጥያቄዎች አቅርበዋል።
አካል ጉዳተኝነትን በአራት ከፍለው ያሳዩት ባለሞያው፣ እነዚኽም አካላዊ፣ ከስሜት ሕዋሳት ጋር የተያያዙ፣ አእምሮአዊ እና የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ጉዳቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ለእነዚኽ ጉዳቶች መሠረታዊ መንስኤዎችም ዘር፣ ወረርሽኝ፣ አደጋ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ሕመም ሊኾኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፤ ነገር ግን ኹሉም ዓይነት አካል ጉዳቶች በዓይን የሚታዩ አለመኾናቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም አካል ጉዳተኝነት ሌሎች ሰዎች ጋር የሚታይ ቢኾንም፣ በማናቸውም ጊዜ በእያንዳንዳችን ላይ ሊከሰት የሚችል ስለኾነ በሀገር ደረጃ ዋነኛ አጀንዳ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል፣ ለዚኽም ኢኮኖሚያዊ እና አኀዛዊ፣ ሞራላዊ እንዲኹም ሕጋዊ ምክንያቶች መኖራቸውን በማስረጃ አስደግፈው አሳይተዋል።
በኢትዮጵያ በተደረጉ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራዎች አካል ጉዳተኝነት በሚል የተካተቱት ጉዳዮች ውስን በመኾናቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአካል ጉዳት ጋር ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱ ሰዎች ቁጥር እዚኽ ግባ የሚባል እንዳልኾነ ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ምጣኔ የተጠኑ ጥናቶች ግን 17.6 በመቶ ሕዝቧ ከአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ያሳያል ብለዋል። ለንጽጽርም የአካል ጉዳተኝነት ምጣኔ በአሜሪካ 26 በመቶ እንዲኹም በእንግሊዝ 22 በመቶ መኾኑን ጠቅሰዋል።
አካታችነትን አስመልክቶ ባነሡት ሐሳብ ከአካል ጉዳት ጋር ለሚኖሩ ሰዎች መሠረታዊው ፈተና አካል ጉዳተኛ መኾናቸው ሳይኾን፣ ኅብረተሰቡ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው ግንዛቤ መኾኑን በአጽንኦት የገለጹት ዶ/ር ዳኛቸው፣ በዚኽም የተነሣ 95 በመቶ የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች ፍጹም ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።
ስለኾነም ኅብረተሰቡ አካል ጉዳተኝነትን የተለየ አድርጎ ማሰብ እንደሌለበት፣ የአካል ጉዳተኛ መብቶችን ማክበር እና የሚገባቸውን ድርሻ ማካፈል ከኹላችንም የሚጠበቅ ሓላፊነት ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ ያሉ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ ብሎም ሀገራዊ የሕግ ማእቀፎችን ዘርዝረው አስረድተዋል። በየመሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ማካተት የግድ እንደኾነ እና ማግለልን መዋጋት የኹሉም ዜጋ ግዴታ መኾኑን ጠቁመዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በቅድመ ምዘና ላይ ለተነሡት ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች ከሥልጠናው በኋላ ቀርበው የመማማሪያ መድረክ ኾነዋል፤ ሠልጣኞች በየመካከሉ ጥያቄ እና መልስ በመስጠት፣ ተሞክሮአቸውን በማካፈል እና እርስ በርስ በመማማር የጎላ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር መርሐ ግብር አስተባባሪ ፍቅርተ ሹመት፣ ለአሠልጣኙ እንዲኹም በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ ለነበሩት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር አባል ድርጅቶች እና ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳዎች ለመጡ ሴት አደረጃጀት መሪዎች ምስጋና አቅርበው ሥልጠናው ተጠናቅቋል።