Timran

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል-ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

የዝግጅት ምዕራፍ አካል የሆኑትን የተሳታፊ መረጣና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ የ2015 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ለመጨረስ እየተሠራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታን በሚያካሂድበት ወቅት ግልጽነት፣ አካታችነት፣ ፍትሐዊ ውክልና፣ አዳዲስ ከዋኞችና ተባባሪዎች እንዲሁም በቂ ጊዜ ታሳቢ እንደሚደረጉ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማኅበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ (ልዩ ወረዳ) አስተዳደር ተወካዮች በተሳታፊ ልየታ ተባባሪነት ተመርጠዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ሲሆን እነሱም፤ ራሳቸውን የሚገልጹበት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው ሰዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች /አባቶች/ እናቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የእጅ ባለሙያዎች፣ የንግድ ማኅበረሰብ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ የሆኑት የአጀንዳ መሰብሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

በየአካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በያሉበት የመጠለያ ስፍራ እንደ 10ኛ ባለድርሻ አካል የራሳቸውን ተወካዮች የሚያመጡበትን አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በእነዚህ አካባቢዎች የተጀመረው የልየታ እና የማሰባሰብ ሥራ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።

ዜጎች በየትኛውም መንገድ አልተወከልንም ብለው ካሰቡ አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ በአካል፣ በፖስታ፣ በስልክ፣ በበይነ መረብ የሚያስገቡበት አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የምክክር ዝግጅቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከየአካባቢው አስተዳደሮች ጋር ውይይት በማድረግ በጋራ ለመሥራት መግባባት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ሰላም እንደሚፈልግ እና ጥያቄዎቹንም በውይይት የመፍታት ፅኑ አቋም እንዳለው ተረድተናል በማለት ገልጸዋል።

ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም በምክክሩ አስፈላጊነት እና አካሄድ ላይ ውይይት አድርጎ ወደ ሥራ ለመግባት ደብዳቤ ተጽፎ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰብና የመረጣ ሥራ አስቸጋሪ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር የ2015 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

ይህን በስኬት በማጠናቀቅ በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ከየወረዳዎች 50 ሰዎችን በተሳታፊነት እንደሚልክ ጠቅሰው በሀገራዊ ምክክሩ እስከ 700 ሺህ ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ሊሳተፉ እንደሚችሉም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ለሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁለት ሁለት ተወካዮችን ይመርጣሉ ብለዋል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ለኮሚሽኑ እያደረጉ ያሉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። (ምንጭ:-ኢዜአ)

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts