Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ለአሪ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጠ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ አሪ እና ደቡብ ኦሞ ምድብ ለሚገኙ ሴቶች ግንቦት 27፣ 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል።

ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል በተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ከአሪ ዞን ልዩ፣ ልዩ ወረዳዎች እንዲኹም ከደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ፣ ሐመር፣ ማሌ፣ ኛንጋቶም፣ ዳሰነች ወረዳዎች እና ቱርሚ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ተወካይ ሴቶች ተሳታፊ ነበሩ።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጥምረቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከምሥረታው ጀምሮ ባለፉት ኹለት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ገልጸዋል።

በዋናነት ጥምረቱ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በዘጠኝ ክልሎች ተመሳሳይ የሴቶች አቅም ግንባታ መድረኮች በማዘጋጀት አጀንዳዎቻቸውንአሰባስቦ ለሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደኾነ ገልጸው፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዐሥረኛው የሴቶች ምክክር መዳረሻ ነው ብለዋል።

ጥምረቱ የአስተባባሪነት ሥልጠና ከሰጣቸው ሠልጣኞች መካከል የኾኑት አካልነሽ ቦጋለ፣ ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ ከሌሎች የችግር መፍቻ መንገዶች ጋር ስላለው ግንኙነት እና የምክክር አስፈላጊነት ለተሳታፊዎች ገለጻ ሰጥተዋል። በምክክር ሂደት ውስጥ ሥርዓተ ጾታን ማካተት አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመው፣ በዋናነት ሴቶች በየትኛውም የሰላም ግንባታ ሂደት ተሳታፊ ሊኾኑ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ገለጻውን ተከትሎ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መሰል እድል አግኝተው እንደማያውቁ ገልጸው፣ ጥምረቱ የሴቶች ድምፅ እንዲሰማ ለማድረግ እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚያም የየዕለቱ ተሳታፊዎች ከየመጡበት ምድብ እና ከየወከሉት ወረዳ አኳያ የአሪ ዞን ሴቶች አርሶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኛ እና አካል ጉዳት ጋር የሚኖሩ ሴቶች፣ የሴቶች ማኅበራት እና ወጣቶች እንዲኹም ሐመር፣ ማሌ፣ ወባ አሪ፣ ኛንጋቶም እና ዳሰነች በሚል ምድብ ተከፍለው ሐሳቦችን አንሸራሽረዋል።

የየምድቡ ተወካዮች በቡድን ውይይት ወቅት ካነሧቸው ሐሳቦች መካከል ቀዳሚ የሚሏቸውን የምድብ አምስት አጀንዳዎች ለመድረኩ ያቀረቡ ሲኾን፣ የቀረቡት አጀንዳዎች በየፈርጃቸው እና በየዞናቸው ተጠቃልለው በጋራ ስምምነት ጸድቀዋል።

በአሪ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በተካሄዱ ሦስት የምክክር መድረኮች ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች የመጡ ከ100 በላይ ሴቶች ተሳትፈዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ሲያካሂድ የቆየውን የሴቶች አቅም ግንባታ መድረክ ቀጣይ ሳምንት ያጠናቅቃል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts