ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ መተከል ዞን አመራሮች ጋር የመክፈቻ ምክክር በግልገል በለስ ከተማ ሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም አከናወነ።
በምክክር መድረኩ ላይ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋወያ፣ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ግዛቱ ባልዳ፣ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ጊሳ ዝህፋን ጨምሮ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
የምክክር መድረኩን የመተከል ዞን የሴቶች ማኅበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ነገሬ ፉፋ በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሴቶች ማኅበር የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አባል መሆኑን ገልጸው፣ መድረኩ የዞኑ ሴቶች ትርጉም ባለው መልኩ በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት የሆነችው ትምራን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን በመድረኩ ላይ በርቀት መተግበሪያ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ጥምረቱ ላለፈው አንድ ዓመት ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ትርጉም ባለው መንገድ እንዲሳተፉ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሴቶች አጀንዳቸውን እንዲለዩ ለማገዝ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና የመጀመሪያው ሀገራዊ መድረክ በድሬዳዋ ከተማ መከናወኑንም ገልጸዋል።
ሁለተኛው መድረክ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንደሚካሄድ እና ከአንድ ወር በፊት በክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ ውስጥ የመክፈቻ መርሐ ግብር መከናወኑን ጠቁመዋል።
በመተከል ዞን የሚከናወነው የምክክር መድረክ ከዞኑ አመራሮች ጋር የትውውቅ እና በቀጣይ ተከታታይ ቀናት ከተለያዩ ወረዳዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ላይ ተሳታፊ ሴቶችን ቅድመ ሁኔታዎች ማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።
የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ የምክክር መድረኩ ማስጀመሪያ መነሻ ሐሳብ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ጥምረቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያከናወናቸውን ዋና፣ ዋና ተግባራት በዝርዝር ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናትም በመተከል ዞን ምድብ ውስጥ ከሚገኙት ዳንጉር፣ ፓዊ፣ ማንዱራ፣ ወምበራ፣ ድባጤ እና ጉባ ማንኩሽ ወረዳዎች እንዲሁም ግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።
በቀረቡት መነሻ ሐሳብ ላይ የዞኑ አመራሮች ሐሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል። በዚህም ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በክልል ደረጃ ከተካሄደው መድረክ በተጨማሪ ለመተከል ዞን አመራሮች የመክፈቻ መርሐ ግብር በማዘጋጀቱ አመስግነዋል።
ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ 50 በመቶ በላይ ቁጥር ያላቸው መሆኑን ብሎም ድምፃቸው ለሀገር እድገት እና ብልጽግና አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ መኖር ለሰላም እና ደኅንነት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናት ከተለያዩ ወረዳዎች ከሚመጡ ተሳታፊዎች ጋር የሚካሄዱ ውይይቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ የመተከል ዞን አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የጥምረቱ አባል ድርጅቶች መካከል የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር አባል እና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሴቶች ማኅበር፣ ሙጀጀዋ ሎካ የሴቶች ማኅበር እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ቅርንጫፍ ተሳታፊ ሆነዋል።

የትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ በሲቪክ ማኅበራት ብሔራዊ የጥናት ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቀረቡ
የትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ማኅደር ዳዲ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የሲቪክ