ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት አቅም ለመፍጠር የአራት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሐረር ከተማ መስጠት ጀመረ።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ስለ ጥምረቱ የአንድ ዓመት ቆይታ እና ክንውኖች ለተሳታፊዎች ገለጻ አቅርበዋል።
ጥምረቱ ትምራንን ጨምሮ በ22 አባል ድርጅቶች ተመሥርቶ በአኹኑ ወቅት ከ50 በላይ አባል ድርጅቶች ያሉት መሆኑንና በሰባት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ምክር ቤት፣ ተርካንፊ ዘላቂ ልማት እና የኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ጥምረቱን በሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ መሆኑንና ትምራን በጽ/ቤት እየሠራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ጥምረቱ በየደረጃው በሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች ውስጥ የሴቶች ውክልና እና ተሳትፎ ትኩረት እንዲሰጠው፣ በሀገር ደረጃ ሴቷ ድምጿ እንዲሰማ እና የራሷ አጀንዳ ያላት መሆኑ እንዲታወቅ የውትወታ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በሐረሪ ክልል ከሚገኙ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል እና አሶሳ ዞኖች ቀጥሎ እየተከናወነ ያለ መርሐ ግብር መሆኑን አመልክተዋል።
በመኾኑም የመድረኩ ተሳታፊ ሴቶች የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሐረሪ ክልልን ጨምሮ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በቅርቡ በሚጀምረው ምክክር ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ እንደሚያግዝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ በሐረሪ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ነዋሪ ከኾኑት መካከል የተመረጡ ሴቶች በሦስት ምድብ ተደልድለው ሥልጠና የሚወስዱ ሲኾን፣ በክልል ደረጃ የአንድ ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር እንደሚኖር ተናግረዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የመጀመሪያ ቀን ላይ ከኤረር፣ አሚር ኑር እና አባድር ወረዳዎች የተውጣጡ ከ140 በላይ የቤት እመቤቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደር ሴቶች፣ የእድር እና አፎቻ አባላት እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች እና የማኅበራት ተወካይ ሴቶች ተሳትፈዋል።