Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በሐረሪ ክልል የጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሦስተኛ ቀን ሥልጠና ተካሄደ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል በሐረሪ ክልል የጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሦስተኛ ቀን ሥልጠና ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሄደ።

በሦስተኛው ቀን ሥልጠና አቦከር፣ ሸንኮር እና ድሬ ጢያራ የተሰኙ የክልሉ ወረዳዎች ነዋሪ የኾኑ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 150 ገደማ ሴቶች ተሳትፈዋል።

በዚኽም መሠረት አካል ጉዳተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ የእድር እና አፎቻ አባላት፣ የቤት እመቤቶች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሲቪክ ማኅበር አባላት እና ወጣት ሴቶች ሥልጠናውን ወስደዋል።

የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ለተሳታፊዎቹ እንኳን ደኅና መጣችኹ ካሉ በኋላ፣ ስለ ጥምረቱ አመሠራረት፣ መሥራች ድርጅቶች፣ ጥምረቱን የሚመሩ ሰባት ሥራ አስፈጻሚ ድርጅቶች፣ ጥምረቱን በጽ/ቤትነት እያገለገለች ያለችው ትምራን እና ለጥምረቱ ያከናወነቻቸውን ተግባራት እና ጥምረቱ ከተመሠረተ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የፈጸማቸውን ሥራዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመቀጠል ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በአመቻችነት ሥልጠና የሰጣቸው ባለሞያዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ የአተገባበር ሂደት፣ አካታችነት እና በምክክር ወቅት የውሳኔ አሰጣጥ ስልቶች ላይ ገለጻ ሰጥተዋል።

የመግቢያ ገለጻውን ተከትሎ ተሳታፊ ሴቶች በየመጡበት ምድብ በጋራ ሆነው ሐሳቦች አንሸራሽረዋል፤ መድረክ ላይ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው ጠቃሚ መኾኑን በሰጡት አስተያየት የገለጹ ሲኾን፣ የጋራ ጉዳያቸውን መለየት የሚችሉበት እና በሀገራዊ ምክክር መድረኩ መሳተፍ የሚችሉበትን ግንዛቤ እንደጨበጡ ተናግረዋል።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ሴቶች በርካታ ሓላፊነቶችን ትተው በመምጣት በመሳተፋቸው እና ለነበራቸው ንቁ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል። እናቶችም ምርቃት ሰጥተው የሥልጠና መርሐ ግብሩ ተጠናቅቋል።

በሐረሪ ክልል የወረዳ ተሳታፊዎች መጀመሪያ ቀን ከኤረር፣ አባድር እና ኢሚር ኑር ወረዳዎች የተውጣጡ 140 በላይ ሴቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲኾን፣ በተመሳሳይ መልኩ በሁለተኛ ቀን ውሎ ከሶፊ፣ ሐኪም እና ጂኔላ ወረዳዎች የተውጣጡ 150 የሚደርሱ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫው መርሐ ግብር ተሳታፊ ነበሩ።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መጋቢት 08 ቀን 2014 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ የሴቶችን መብቶች ለማስጠበቅ በሚሠሩ 22 ሲቪክ ማኅበራት የተቋቋመ ሲኾን፣ ዓላማው ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና የሴቶችን ፍላጎቶች፣ ቀዳሚ ጉዳዮች እና ምኞቶች እውን እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

በአንድ ዓመት ቆይታ ውስጥ ጥምረቱ ከ50 በላይ አባላት ያፈራ ሲሆን፣ ሰባት ሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት እና ሴክሬታሪያት አሉት። ትምራን የጥምረቱ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

የጥምረቱ አባላት ተጠሪነታቸው ለሴክሬታሪያት፣ ለሥራ አመራሩ እና ለራሱ ለጥምረቱ ሲሆን የጥምረቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች የማከናወን ሥልጣን አላቸው።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts