Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በኦሮሚያ ክልል ያካሄዳቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረኮች ማጠቃለያ መርሐ ግብር አካሄደ ከምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ቄለም እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ምድብ ለመጡ ሴቶች ሥልጠና ተሰጥቷል

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በኦሮሚያ ክልል ያካሄዳቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረኮች ማጠቃለያ መርሐ ግብር መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አካሄደ።

ከማጠቃለያው መርሐ ግብር አስቀድሞ የክልሉ ሰባተኛ ምድብ የኾነው ከምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ቄለም እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ምድብ ለመጡ ሴቶች መጋቢት 03 ቀን 2016 ዓ.ም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷል። በዚኽ ምድብ ሥልጠና ላይ 40 ገደማ ሴቶች ተሳትፈዋል። የዕለቱን ሥልጠና በንግግር የከፈቱት የጥምረቱ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል በ22 የሲቪክ እና የሴቶች ማኅበራት የዛሬ ሁለት ዓመት መመሥረቱን ገልጸዋል።
ጥምረቱ ዘጠኝ አባላት ባሉት ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ መኾኑንና ትምራን ከምሥረታው ጀምሮ በጽ/ቤትነት በማገልገል ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በአኹኑ ወቅት ጥምረቱ 60 ገደማ አባል ድርጅቶች ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መኾኑንም አመልክተው፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ተመሳሳይ የሥልጠና መድረኮች በዘጠኝ ክልሎች ማከናወኑን ተናግረዋል።

በመቀጠል የዕለቱ የሥልጠና አስተባባሪ የነበሩት ድንቄ ከድር የምድቡ ተሳታፊ ሴቶች ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች፣ የሥርዓተ ጾታ ምንነት፣ አካታችነት እና የድምፅ መስጫ ስልቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ገልጸዋል። ከዚያም ተሳታፊዎች ከየመጡበት የማኅበረሰብ ክፍል አኳያ ነጋዴ እና አካል ጉዳተኛ ሴቶች፣ የመንግሥት ሠራተኛ እና ወጣት ሴቶች፣ የፍትሕ አካላት እና አርሶ አደር ሴቶች፣ የቤት እመቤት እና ሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና የሴቶች ማኅበር ተወካዮች በሚል ቡድን ተወያይተው ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል።

መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሰሎሞን፣ ስለ ጥምረቱ አመሠራረት ሂደት አጭር ገለጻ ሰጥተው፣ ጥምረቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማእከል፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብቶች ተሟጋች፣ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ ተርካንፊ ለዘላቂ ልማት እና ኡጋሶ ውሜን ዲያሎግ ስፔስ በተባሉ ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚ ድርጅቶች የሚመራ መኾኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ መድረኮችን ለማዘጋጀት ትምራን ስትንቀሳቀስ አብረው በመሥራት መድረኮቹ እንዲሳኩ ያደረጉትን የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን፣ የኦሮሚያ ሴቶች ማኅበር፣ ተርካንፊ ለዘላቂ ልማት እና ሲቄ የሴቶች ልማት ድርጅት ብሎም የገንዘብ እገዛ የሰጠውን አይሪሽ ኤይድ አመስግነዋል።

የመድረኩን ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዕፀገነት ኃይሌ፣ ጥምረቱ በክልሉ ያሉ ችግሮች ሳያግዱት በጽ/ቤቱ ትምራን በኩል ከኦሮሚያ ሴቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ያሳየውን በጎ ፈቃድ አድንቀው በቀጣይ በጋራ ብዙ ሥራዎች ይሠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ጥምረቱ ያዘጋጀው የኦሮሚያ ክልል የማጠቃለያ መድረክ ተሳታፊ የኾኑ 50 ገደማ ሴቶች በቀጣይ ወደማኅበረሰባቸው ሴሄዱ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙም አሳስበዋል።

ይኽንን ተከትሎ የማጠቃለያ መድረኩ ተሳታፊ የነበሩት 50 ገደማ ሴቶች በቡድን ተከፍለው የየራሳቸውን አጀንዳዎች ቀርፀው አቅርበዋል፤ ከዚያም በክልሉ ውስጥ በሌሎች ስድስት የሴቶች ምድቦች ላይ የተነሡ የተጠቃለሉ ሐሳቦች ቀርቦላቸዋል።

በመድረኩ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት (ተጠባባቂ) ወሮ አስካለ ለማ፣ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱት ምክክሮች በቂ ናቸው ባይባልም ጥሩ ግብአት የተገኘባቸው ናቸው ብለዋል። በቀጣይ ጥምረቱ በየክልሉ ከሚገኙ የሴቶች አደረጃጀት ጋር ተከታታይ ሥራዎች ሊሠራ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከየካቲት 07 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ባካሄዳቸው ሰባት የምድብ እንዲኹም የመክፈቻ እና መዝጊያ መርሐ ግብሮች ላይ በድምሩ 500 ሴቶችን መድረስ ችሏል።

ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ደግሞ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ሐረሪ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊ፣ አፋር እና ኦሮሚያ በድምሩ በዘጠኝ ክልሎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሴቶች ድምፅ ተገቢ ውክልና እንዲሰጠው ለማስቻል ከ4000 በላይ ለኾኑ ሴቶች የሥልጠና መድረኮችን አዘጋጅቷል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts