Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከተለያዩ ክልሎች ያሰባሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች ማጠናቀር ጀመረ


ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል ከኹለት ዓመታት በፊት ተመሥርቶ በአኹኑ ወቅት 60 ገደማ ድርጅቶችን በማስተባበር የሚንቀሳቀሰው ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከሰባት ክልሎች እና ኹለት ከተማ አስተዳደሮች ያሰባሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ማጠናቀር ጀመረ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ጥምረቱን በጽ/ቤትነት የምታገለግለው እና ሴቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ እና ውሳኔ ሰጭነት ውስጥ እኩል ተሳታፊ እንዲኾኑ ራእይ ሰንቃ የምትሠራው ትምራን የተሰኘችው ሀገር በቀል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን ናቸው።

ሥራ አስኪያጇ ጥምረቱ ስለተቋቋመበት ዓላማ፣ ምሥረታውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ ውይይቶች እና በሀገራዊ ምክክሩ ተሳትፎ ውስጥ የሴቶች ኮታ 50 በመቶ እንዲኾን፣ አጀንዳዎቻቸው እንዲካተቱ፣ የክትትል እና ግምገማ ሥራ እንዲሠራ ብሎም ለዚኹ ዓላማ የሀብት ማፈላለግ ተግባራት እንዲያከናውን በወቅቱ መግባባት ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

በዚኽም መሠረት ጥምረቱን የሚመራው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ጥር 2015 ዓ.ም ላይ ከመላው ሀገሪቱ ለተውጣጡ 151 ሴቶች ሀገራዊ ምክክር እና የሴቶች ተሳትፎ የተመለከተ የአስተባባሪነት የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ጥምረቱ ባደረጋቸው ጥረቶች በሀገር ደረጃ የሚከናወኑ የምክክር ሂደቶች ውስጥ ሴቶች አንድ ምድብ እንዲኖራቸው፣ በየደረጃው 30 በመቶ ኮታ እንዲያገኙ፣ ጥምረቱ የአስተባባሪነት ሥልጠና ከሰጣቸው መካከል 28 ሴቶች ኮሚሽኑ በሚያካሂዳቸው ምክክሮች ውስጥ በአስተባባሪነት እንዲመረጡ ማድረጉን ጠቁመዋል-ሥራ አስኪያጇ።

ይኽንን ተከትሎ ከመጋቢት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በሐረሪ፣ ቢኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ 4000 ገደማ ሴቶች አይሪሽ ኤይድ እና ዩኤስኤይድ/ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት ከተሰኙ መያዶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን ማሰባሰቡን ገልጸዋል።

የመድረኩም ዓላማ በመጀመሪያ ዙር የተሰባሰቡትን እነዚኽን የሴቶች ሐሳቦች በማጠናቀር በሀገር ደረጃ ጎልተው የወጡ የሴቶችን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከብ መኾኑን ተናግረዋል።

በቀጣይነት በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎች ለሚገኙ ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣ የሴቶች አጀንዳዎች ወደፊት እንዲመጡ የውትወታ ሥራዎች ማጠናከር፣ በሀገር ደረጃ በሚደረጉ የምክክር መድረኮች ተሳታፊ ለሚኾኑ ሴቶች ሥልጠና ማዘጋጀት ጨምሮ ጥምረቱ በቀጣይ ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ተግባራት ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ ቁልፍ ተናጋሪ የነበሩት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ድባቤ ባጫ በበኩላቸው፣ ጥምረቱ የሴቶችን አጀንዳ በተስተካከለ መልኩ ለማሰማት መቋቋሙንና ባለፉት ኹለት ዓመታት በርካታ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

የጥምረቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ደግሞ፣ የመድረኩ ተሳታፊ ለኾኑት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የሥራ ክፍል ተጠሪዎች እና ባልደረቦች ጥምረቱ የነበረውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ገለጻ አቅርበዋል።

ለአራት ቀናት የሚቆየው መድረክ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የሴቶችን አጀንዳዎች ለማጠናቀር በተቀጠረው አማካሪ ድርጅት በኩል የቀረቡ መነሻ ሐሳቦች ላይ ውይይት በማድረግ የአጀንዳ ማጠናቀር መስፈርቶች፣ መለኪያዎች እና ነጥብ አሰጣጥ ላይ መግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቅቋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts