Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ለአራት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቀቀ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ለአራት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቀቀ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲረጋገጥ ለማስቻል ለአራት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሠኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተጠናቀቀ።

በመድረኩ ላይ ከክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች እና ወረዳዎች የተውጣጡ 50 ገደማ ሴት ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የማጠቃለያ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ በተገቢው መንገድ ውክልናቸውን ለማረጋገጥ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ 50 በላይ አባል ድርጅቶችንና ሲቪክ ማኅበራትን የያዘ ስብስብ መኾኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ቀናት በሲዳማ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከ30 በላይ ወረዳዎች የተውጣጡ 500 ያኽል ሴቶች በሦስት ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በአራተኛው ቀን የማጠቃለያ መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሴቶች በዕለቱ በተሰጠው የሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ አካታችነት፣ ከምክክር በኋላ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የተመለከቱ ጉዳዮችን በያዘው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ማብራሪያ መሠረት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንሥተዋል፤ በአምስት ምድብ ተከፍለው የቡድን ሥራ ላይ ተሳትፈዋል፤ ለተሳታፊዎች የየቡድናቸውን ሐሳብ አቅርበዋል።

በመቀጠል ከሐዋሳ ዙሪያ፣ ከይርጋለም እና ሀገረ ማርያም ምድብ የተውጣጡ ሴቶች ከሠኔ 12-14 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ሦስት ቀናት በየቡድናቸው ያነሧቸው ሐሳቦች ቀርበውላቸው ሐሳብ እና አስተያየት ሰጥተው አጽድቀዋል።

በመድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡት ሴቶች ጥምረቱ ለአራት ቀናት ያዘጋጀው መድረክ እጅግ ጠቃሚ እንደነበር፣ በክልሉ ሴቶች የተነሡት ሐሳቦች የጋራነት ያላቸው መኾኑ ሴቶች እኩል እንደሚያስቡ እና የመፍትሔ አካል መኾናቸውን ያመላከተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አስቻለው የማጠቃለያ መድረኩን ሲዘጉ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ባለፉት ወራት በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ክልሎች ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ በሲዳማ ክልል የተካሄደው መድረክ አራተኛ መኾኑን ጠቁመዋል።

አያይዘውም ጥምረቱ በመላው ሀገሪቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማከናወን በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች ድምፅ በተገቢው መልኩ እንዲሰማ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ጠቅሰው፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮች ለማከናወን ደጋፊ አካላት እየተጠባበቀ ነው ብለዋል።

በሲዳማ ክልል በተከታታይ አራት ቀናት በተካሄዱት የምክክር መድረኮች ላይ በጠቅላላው ከ500 በላይ ሴቶች ተሳታፊ ኾነዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts