Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት አቅም ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት ጀመረ


ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን ውስጥ ከሚገኙት አሶሳ 1፣ አሶሳ 2፣ አብርሃሞ፣ ኡዱሉ፣ ባምባሲ እና ዑራ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የሦስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በአሶሳ ከተማ ከግንቦት 09 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት ጀመረ።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩ የመጀመሪያ ቀን ላይ ቁጥራቸው ከ140 በላይ የሚሆኑ የቤት እመቤቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ ነጋዴዎች፣ የማኅበራት ተወካዮች፣ አርሶ አደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና በፍትሕ አካላት ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች ተሳትፈዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በንግግር የከፈቱት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ ከአንድ ዓመት በፊት ትምራንን ጨምሮ በ22 አባል ድርጅቶች ተመሥርቶ በአኹኑ ወቅት ከ50 በላይ የሆኑ አባል ድርጅቶችን ያቀፈ ጥምረት መሆኑንና ከአባል ድርጅቶች በተውጣጡ ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥምረቱን በሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ የሚገኙት አባል ሲቪክ ማኅበራት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ምክር ቤት፣ ተርካንፊ ዘላቂ ልማት እና የኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር መሆናቸውን ጠቁመው፣ ትምራን የጥምረቱ ጽ/ቤት ሆና እያገለገለች መሆኑን ገልጸዋል።

ጥምረቱ በየደረጃው በሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች ውስጥ የሴቶች ውክልና እና ተሳትፎ ትኩረት እንዲሰጠው፣ በሀገር ደረጃ ሴቷ ድምጿ እንዲሰማ እና የራሷ አጀንዳ ያላት መሆኑ እንዲታወቅ የውትወታ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመተከል ዞን የተሰጠው የሴቶችን አቅም የማጎልበት ሥልጠና ጥምረቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያከናውናቸው መድረኮች መካከል አንዱ እንደሆነ እና በመድረኩ ላይ የሚነሡ ሐሳቦች ሴቶች ወደፊት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚያደርገው ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማገዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር፣ በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የማንቃት እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥልጠና በየክልሎች እንደሚያዘጋጅም አመልክተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ በአሶሳ ዞን ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች በሦስት ምድብ ተከፍለው እንደሚወስዱ ታውቋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts