Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ከሲዳማ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች የሀገራዊ ምክክር ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማካሄድ ላይ ነው

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በሲዳማ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ተገቢ ውክልና ለማረጋገጥ እንዲቻል የአራት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ሠኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ በመላው ሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ከ50 በላይ የሆኑ ሲቪክ ድርጅቶች እና የሴቶች ማኅበራት አባላት ያሉት መኾኑንና በሰባት ሥራ አመራር ኮሚቴ ድርጅቶች የሚመራ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የጥምረቱ ሥራ አመራር ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር፣ ተርካንፊ ለዘላቂ ልማት፣ የአማራ ሴቶች ማኅበር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማኅበር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ማእከል ናቸው።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እና በሁሉም ዘርፍ ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዲመጡ ማስቻል ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራው ትምራን የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ አባል ድርጅት የኾነችው ጽ/ቤት በመኾን እያገለገለች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።

ጥምረቱ ቀደም ሲል ከአይሪሽ ኤይድ በተገኘ ድጋፍ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ መድረክ ማዘጋጀቱን መጠቁመው፣ በዩኤስይድ ስር በሚንቀሳቀሰው ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ ቀደም ሲል የተከናወኑትን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ክልሎችን ጨምሮ የሲዳማ ክልል ሦስተኛው መድረክ እንደኾነ ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል በተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የመጀመሪያ ቀን ከጎርቼ፣ ሸበዲኖ፣ ቦርቻ፣ ለኩ፣ ደራራ፣ ብላቴ፣ መልጋ፣ ሐዋሳ ዙሪያ፣ ወንዶ ወረዳ እና ወንዶ ከተማ የተውጣጡ 163 ሴቶች ተሳታፊ ኾነዋል።

ሠኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው መድረክ ደግሞ ሎካ፣ ወንሾ፣ ዳሌ፣ ይርጋ ዓለም ከተማ፣ አለታ ወረዳ፣ አለታ ከተማ፣ አለታ ጨኮ ወረዳ እና ጩኮ ከተማ የተውጣጡ ከ150 በላይ ሴቶች ተሳትፈዋል።

በሁለቱ ቀናት መድረኮች ላይ ከቤት እመቤት፣ አካል ጉዳተኛ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣ ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ሴቶች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ ከተለያዩ ማኅበራት፣ ፌዴሬሽን እና በፍትሕ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች ተሳታፊ ኾነዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ እስከ ሠኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲኾን በጠቅላላው 500 የሚደርሱ የክልሉ ሴቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts