Timran

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ከመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት አቅም ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና አከናወነ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በሦስት ምድብ ማለትም ምድብ አንድ ጉባ ማንኩሽ ወረዳ፤ ምድብ ሁለት ዳንጉር፣ ፓዊ እና ማንዱራ ወረዳዎች እንዲሁም ምድብ ሦስት ከድባጤ፣ ወምበራ እና ቡለን ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የሦስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በግልገል በለስ ከተማ አከናወነ።

በምድብ አንድ ጉባ ማንኩሽ ወረዳ ለተውጣጡ 50 ለሚሆኑ የቤት እመቤቶች፣ ሴት አካል ጉዳተኞች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ ሴት የመንግሥት ሠራተኞች፣ በፍትሕ አካላት ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች፣ የማኅበራት ሴት ተወካዮች እና ወጣት ሴቶች ሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩ ተሰጥቷል።

በምድብ ሁለት ውስጥ ለሚገኙት ዳንጉር፣ ፓዊ እና ማንዱራ ወረዳዎች ለተውጣጡ 150 ገደማ ለሚሆኑ ሴት አርሶ አደሮች፣ ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች፣ የቤት እመቤቶች፣ ሴት አካል ጉዳተኞች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ ሴት የመንግሥት ሠራተኞች፣ በፍትሕ አካላት ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች፣ የእቁብ እና እድር አባላት ሴት ተወካዮች እና ወጣት ሴቶች ደግሞ ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ሥልጠናው ተከናውኗል።

በምድብ ሦስት ማለትም ከድባጤ፣ ወምበራ እና ቡለን ወረዳዎች ለተውጣጡ ከ140 በላይ ሴቶች ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ተሰጥቷል።

ለሦስት ቀናት የተሰጡ ሥልጠናዎችን በንግግር የከፈቱት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ ትምራንን ጨምሮ ከ50 በላይ የሆኑ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበር አባል ድርጅቶችን ያቀፈ ጥምረት መሆኑንና ከሰባት አባል ድርጅቶች በተውጣጡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥምረቱን በሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ የሚገኙት አባል ሲቪክ ማኅበራት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ምክር ቤት፣ ተርካንፊ ዘላቂ ልማት እና የኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር መሆናቸውንና ትምራን የጥምረቱ ጽ/ቤት እንደሆነች ጠቁመዋል።

ጥምረቱ በየደረጃው በሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች ውስጥ የሴቶች ውክልና እና ተሳትፎ ትኩረት እንዲሰጠው፣ በሀገር ደረጃ ሴቷ ድምጿ እንዲሰማ እና የራሷ አጀንዳ ያላት መሆኑ እንዲታወቅ የውትወታ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመተከል ዞን የተሰጠው የሴቶችን አቅም የማጎልበት ሥልጠና ጥምረቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያከናውናቸው መድረኮች መካከል አንዱ እንደሆነ እና በመድረኩ ላይ የሚነሡ ሐሳቦች ሴቶች ወደፊት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚያደርገው ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማገዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር፣ በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የማንቃት እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥልጠና በየክልሎች እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።
ለሦስት ቀናት በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የተገኙ ሴት ተሳታፊዎች ከሥልጠናው ጥሩ ግብአት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር በቀጣይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ እና ከማሺ ዞኖች ለሚውጣጡ ሴቶች ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።

Share this post on

Share on facebook
Share on telegram
Share on whatsapp
Share on pinterest
Share on twitter
Share on linkedin
Share on skype
Share on print

Latest Posts

Archives


Categories